YouVersion Logo
Search Icon

ሚክያስ 2

2
የእግዚአብሔርና የሰው ዕቅድ
1ክፉ ለመሥራት ለሚያቅዱ፣
በመኝታቸው ሳሉ ተንኰል ለሚያውጠነጥኑ ወዮላቸው!
ሲነጋ በማለዳ ይፈጽሙታል፤
የሚያደርጉበት ኀይል በእጃቸው ነውና።
2ዕርሻ ይመኛሉ፤ ይይዙታልም፤
ቤት ይመኛሉ፤ ይወስዱታልም፤
የሰውን ቤት፣
የባልንጀራን ርስት አታልለው ይወስዳሉ።
3ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ በዚያ ሕዝብ ላይ ጥፋት ላመጣ ዐቅጃለሁ፤
ከዚህም ለማምለጥ አትችሉም።
ከእንግዲህ በትዕቢት አትመላለሱም፤
የመከራ ጊዜ ይሆናልና።
4በዚያ ቀን ሰዎች ይሣለቁባችኋል፤
በሐዘን እንጕርጕሮ እንዲህ እያሉ ያፌዙባችኋል፤
‘እኛ ፈጽሞ ጠፍተናል፤
የወገኔ ርስት ተከፋፍሏል።
ከእኔ ነጥቆ ወስዶ፣
ዕርሻዎቻችንን ላሸነፉን አከፋፈለ።’ ”
5ስለዚህ በእግዚአብሔር ጉባኤ ውስጥ፣
መሬት በዕጣ የሚያካፍል ማንም አይኖርም።
ሐሰተኞች ነቢያት
6ነቢያቶቻቸው፣ “ትንቢት አትናገርብን፤
ስለ እነዚህ ነገሮች ትንቢት አትናገር፤
ውርደት አይደርስብንም” ይላሉ።
7የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ እንዲህ ሊባል ይገባልን?
የእግዚአብሔር መንፈስ የማይታገሥ ነውን?
እንዲህ ያሉ ነገሮችንስ ያደርጋልን?”
“መንገዱ ቀና ለሆነ፣
ቃሌ መልካም አያደርግምን?
8በመጨረሻ በሕዝቤ ላይ ጠላት ሆናችሁ
ተነሣችሁ፤
የጦርነት ሐሳብ ሳይኖራቸው፣
በሰላም ከሚያልፉ ሰዎች ላይ
ማለፊያ መጐናጸፊያ ገፈፋችሁ።
9ከሚወድዱት ቤታቸው፣
የሕዝቤን ሴቶች አስወጣችኋቸው፤
ክብሬን ከልጆቻቸው
ለዘላለም ወሰዳችሁ።
10ተነሡና ከዚያ ሂዱ፤
ይህ ማረፊያ ቦታችሁ አይደለምና፤
ምክንያቱም ረክሷል፤
ክፉኛም ተበላሽቷል።
11ሐሰተኛና አታላይ ሰው መጥቶ፣
‘ስለ ብዙ የወይን ጠጅና ስለሚያሰክር መጠጥ ትንቢት እነግራችኋለሁ’ ቢል፣
ለዚህ ሕዝብ ተቀባይነት ያለው ነቢይ ይሆናል።
የትድግና ተስፋ
12“ያዕቆብ ሆይ፤ በርግጥ ሁላችሁንም እሰበስባለሁ፤
የእስራኤልንም ትሩፍ በአንድነት አመጣለሁ፤
በጕረኖ ውስጥ እንዳሉ በጎች በመሰማሪያ ላይ እንዳለ መንጋ በአንድነት
እሰበስባቸዋለሁ፤
ቦታውም በሕዝብ ይሞላል።
13የሚሰብረው ወጥቶ በፊታቸው ይሄዳል፤
እነርሱም በሩን በመስበር ወጥተው ይሄዳሉ።
እግዚአብሔር እየመራቸው፣
ንጉሣቸው ቀድሟቸው ይሄዳል።”

Currently Selected:

ሚክያስ 2: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy