YouVersion Logo
Search Icon

ሚክያስ 1

1
1በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን ወደ ሞሬታዊው ወደ ሚክያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል፣ ስለ ሰማርያና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ ይህ ነው፤
2እናንተ አሕዛብ ሆይ፤ ሁላችሁም ስሙ፤
ምድር ሆይ፤ በውስጧም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ፤
ጌታ ከቅዱስ መቅደሱ፣
ልዑል እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይመሰክርባችኋል።
በሰማርያና በኢየሩሳሌም ላይ የተላለፈ ፍርድ
3እነሆ፤ እግዚአብሔር ከመኖሪያ ስፍራው ይመጣል፤
ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይራመዳል።
4ተራሮች ከሥሩ ይቀልጣሉ፤
ሸለቆዎችም ይሰነጠቃሉ፤
በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣
በገደል ላይ እንደሚወርድ ፈሳሽ ይሆናሉ።
5ይህ ሁሉ የሚሆነው ስለ ያዕቆብ በደል፣
ስለ እስራኤልም ቤት ኀጢአት ነው።
የያዕቆብ በደል ምንድን ነው?
ሰማርያ አይደለችምን?
የይሁዳስ የኰረብታ መስገጃ ምንድን ነው?
ኢየሩሳሌም አይደለችምን?
6“ስለዚህ ሰማርያን የፍርስራሽ ክምር፣
ወይን የሚተከልባትም ስፍራ አደርጋታለሁ፤
ድንጋዮቿን ወደ ሸለቆ አወርዳለሁ፤
መሠረቷንም ባዶ አደርጋለሁ።
7ጣዖቶቿ ሁሉ ይሰባበራሉ፤
ለቤተ መቅደሷ የቀረበው ገጸ በረከት በእሳት ይቃጠላል፤
ምስሎቿን ሁሉ እደመስሳለሁ፤
ገጸ በረከቷን በዝሙት ዐዳሪነት እንደ ሰበሰበች ሁሉ፣
አሁንም ገጸ በረከቷ የዝሙት ዐዳሪነት ዋጋ መቀበያ ይሆናል።”
ልቅሶና ሐዘን
8በዚህ ምክንያት አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይም እላለሁ፤
ባዶ እግሬንና ዕርቃኔን እሄዳለሁ፤
እንደ ቀበሮ አላዝናለሁ፤
እንደ ጕጕትም አቃስታለሁ።
9ቍስሏ የማይሽር ነውና፤
ለይሁዳ ተርፏል፤
እስከ ሕዝቤ መግቢያ በር፣
እስከ ኢየሩሳሌም እንኳ ደርሷል።
10በጌት#1፥10 ጌት የሚለው ቃል በዕብራይስጡ አውራ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። አታውሩት፤
ከቶም አታልቅሱ#1፥10 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ሲስማማ፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን በአኮ ላይ አታልቅሱ ይላል። በአኮ የሚለው የዕብራይስጡ ቃል አለቀሰ ከሚለው የዕብራይስጡ ቃል ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው።
በቤትዓፍራ#1፥10 ቤትዓፍራ ትርጕሙ የትቢያ ቤት ማለት ነው።
በትቢያ ላይ ተንከባለሉ።
11እናንት በሻፊር#1፥11 ሻፊር ትርጕሙ አስደሳች ማለት ነው። የምትኖሩ፣
ዕርቃናችሁን ሆናችሁ በኀፍረት ዕለፉ፤
በጸዓናን#1፥11 ጸዓናን የሚለው ቃል በዕብራይስጡ ውጣ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። የሚኖሩ
ከዚያ አይወጡም፤
ቤትዔጼል በሐዘን ላይ ናት፤
ለእናንተም መጠጊያ ልትሆን አትችልም።
12ከመከራው መገላገልን በመሻት፣
በማሮት#1፥12 ማሮት የሚለው ቃል በዕብራይስጡ መራራ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። የሚኖሩ በሥቃይ
ይወራጫሉ፤
እስከ ኢየሩሳሌም በር ሳይቀር፣
ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ መጥቷልና።
13እናንት በለኪሶ#1፥13 ለኪሶ የሚለው ቃል በዕብራይስጡ ቡድን ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። የምትኖሩ፣
ፈረሶችን ከሠረገላው ጋር አያይዙ፤
ለጽዮን ሴት ልጅ፣
የኀጢአት መጀመሪያ እናንት ነበራችሁ፤
የእስራኤል በደል
በእናንተ ዘንድ ተገኝቷልና።
14ስለዚህ እናንተ ለሞሬሼትጌት፣
ማጫ ትሰጣላችሁ፤
የአክዚብ#1፥14 አክዚብ ትርጕሙ አታላይ ወይም ማታለል ማለት ነው። ከተማ፣
ለእስራኤል ነገሥታት መታለያ ትሆናለች።
15እናንት በመሪሳ#1፥15 መሪሳ የሚለው ቃል በዕብራይስጡ ድል አድራጊ ከሚለው ጋር ተመሳሳይ አነባበብ አለው። የምትኖሩ
ድል አድራጊ አመጣባችኋለሁ፤
ያ የእስራኤል ክብር የሆነው
ወደ ዓዶላም ይመጣል።
16ደስ ለምትሰኙባቸው ልጆቻችሁ፣
በሐዘን ራሳችሁን ተላጩ፤
ራሳችሁን እንደ አሞራ ራስ ተመለጡት፤
ከእናንተ በምርኮ ይወሰዳሉና።

Currently Selected:

ሚክያስ 1: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy