ማቴዎስ 3
3
የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት
3፥1-12 ተጓ ምብ – ማር 1፥3-8፤ ሉቃ 3፥2-17
1በዚያ ወራት መጥምቁ ዮሐንስ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። 2ስብከቱም፣ “ንስሓ ግቡ፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና” የሚል ነበር። 3በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረለት እርሱ ነው፤
“በምድረ በዳ፣
‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤
ጐዳናውንም አስተካክሉ’ እያለ የሚጮኽ ድምፅ።”#3፥3 ኢሳ 40፥3
4የዮሐንስ ልብስ የግመል ጠጕር ሲሆን፣ ወገቡንም በጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሓ ማር ነበር። 5ከኢየሩሳሌም፣ ከመላው ይሁዳና በዮርዳኖስ ዙሪያ ካለው አገር ሁሉ ሰዎች ወደ ዮሐንስ ይጐርፉ፣ 6ኀጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ በርሱ እጅ ይጠመቁ ነበር።
7ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ወደሚያጠምቅበት ስፍራ ሲመጡ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የእፉኝት ልጆች! ከሚመጣው ቍጣ እንድታመልጡ ማን መከራችሁ? 8እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አፍሩ፤ 9‘አብርሃም አባት አለን’ በማለት አታስቡ፤ እግዚአብሔር ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት እንደሚችል እነግራችኋለሁና። 10እነሆ፤ ምሣር የዛፎችን ሥር ሊቈርጥ ተዘጋጅቷል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል።
11“እኔ ለንስሓ በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ጫማውን መሸከም ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ፣ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ እርሱም በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። 12መንሹ በእጁ ነው፤ ዐውድማውን ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውን በጐተራ ይከትታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”
የኢየሱስ መጠመቅ
3፥13-17 ተጓ ምብ – ማር 1፥9-11፤ ሉቃ 3፥21-22፤ ዮሐ 1፥31-34
13በዚያ ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። 14ዮሐንስ ግን፣ “ይህማ አይሆንም፤ እኔ ባንተ መጠመቅ ሲያስፈልገኝ እንዴት አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ?” ብሎ ተከላከለ።
15ኢየሱስም፣ “ግድ የለም ፍቀድልኝ፤ ይህን በማድረግ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና” አለው፤ ዮሐንስም በነገሩ ተስማማ።
16ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። 17እነሆ፤ “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።
Currently Selected:
ማቴዎስ 3: NASV
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.