YouVersion Logo
Search Icon

ማቴዎስ 2

2
የጠቢባን ከምሥራቅ መምጣት
1በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን፣ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ይሁዳ ከተወለደ በኋላ፣ ጠቢባን ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ 2“የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ#2፥2 ወይም ኮከቡ ሲነሣ አይተን ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” ሲሉ ጠየቁ።
3ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላዪቱ ኢየሩሳሌም አብራ ታወከች። 4እርሱም የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንን በሙሉ ሰብስቦ፣ ክርስቶስ#2፥4 ወይም መሲሕ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። 5እነርሱም፣ “በይሁዳ ቤተ ልሔም፤ ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፏልና አሉ፤
6“ ‘በይሁዳ ምድር የምትገኚው አንቺ ቤተ ልሔም፣
ከሌሎቹ የይሁዳ ገዦች በምንም አታንሺም፤
የሕዝቤ የእስራኤል ጠባቂ የሚሆን፣
ከአንቺ ይወጣልና።’ ”
7ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። 8ጠቢባኑንም ወደ ቤተ ልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው።
9ጠቢባኑ ንጉሡ ያለውን ከሰሙ በኋላ ጕዟቸውን ቀጠሉ። ይህም በምሥራቅ#2፥9 ወይም ሲነሣ አይተው ያዩት ኮከብ እየመራቸው ሕፃኑ እስካለበት ድረስ ወሰዳቸው። 10ኮከቡንም ሲያዩ ከመጠን በላይ ተደሰቱ። 11ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩ፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት። 12እግዚአብሔርም ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ወደ ግብፅ ሽሽት
13ጠቢባኑ ከሄዱ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሥ! የምትመለስበትን ጊዜ እስካስታውቅህ ድረስ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ በመሸሽ በዚያ ቈይ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻልና” አለው።
14ስለዚህም ዮሴፍ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብፅ ሄደ፤ 15በዚያም ሄሮድስ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ኖረ። በዚህም፣ “ልጄን ከግብፅ ምድር ጠራሁት” በማለት እግዚአብሔር በነቢዩ አንደበት የተናገረው ቃል ተፈጸመ።
16ሄሮድስ ጠቢባኑ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ በጣም ተናደደ። ከጠቢባኑ በተነገረው መሠረት፣ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን የቤተ ልሔምንና የአካባቢዋን መንደሮች ወንድ ልጆች ሁሉ ልኮ አስገደለ። 17በዚህም በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤
18“የልቅሶና የታላቅ ዋይታ ድምፅ
በራማ ተሰማ፤
ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤
መጽናናትም አልቻለችም፤
ልጆቿ ሁሉ ዐልቀዋልና።”
ከግብፅ ወደ ናዝሬት
19ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ 20“ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው።
21ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ 22ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ 23ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።

Currently Selected:

ማቴዎስ 2: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy