YouVersion Logo
Search Icon

ዘሌዋውያን 19

19
ልዩ ልዩ ሕግጋት
1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጉባኤ እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።
3“ ‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ ሰንበታቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
4“ ‘ወደ ጣዖታት ዘወር አትበሉ፤ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክት አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
5“ ‘የኅብረት መሥዋዕት#19፥5 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ። 6መሥዋዕቱም ባቀረባችሁት ዕለት ወይም በማግስቱ ይበላ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የተረፈ ማንኛውም ነገር ይቃጠል። 7በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ ተቀባይነትም የለውም። 8ከመሥዋዕቱ የሚበላ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰውን ነገር አርክሷልና ይጠየቅበታል፤ ያም ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ።
9“ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ በዕርሻችሁ ዳርና ዳር ያለውን አትጨዱ፤ ቃርሚያውንም አትልቀሙ። 10የወይንህን ዕርሻ አትቃርም፤ የወደቀውንም አትልቀም፤ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
11“ ‘አትስረቁ፤
“ ‘አትዋሹ፤
“ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታልል።
12“ ‘በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን (ኤሎሂም) ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
13“ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም፤
“ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር።
14“ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
15“ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታዳላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በትክክል ፍረድ።
16“ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ፤
“ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
17“ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው።
18“ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
19“ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ፤
“ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል፤
“ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ፤
“ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።
20“ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋር ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም። 21ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያምጣ። 22ካህኑም በበደል መሥዋዕቱ አውራ በግ፣ ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል።
23“ ‘ወደ ምድሪቱ ገብታችሁ ማንኛውንም ዐይነት ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ፣ ፍሬው ለመብላት የተከለከለ መሆኑን ዕወቁ፤ ለሦስት ዓመትም የተከለከለ#19፥23 ዕብራይስጡ ያልተገረዘ ይላል በመሆኑ አይበላ። 24በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ሁሉ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል። 25በአምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ ፍሬው ይበዛላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
26“ ‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ሥጋ አትብሉ፤
“ ‘ጥንቈላ ወይም አስማት አትሥሩ።
27“ ‘የራስ ጠጕራችሁን ዙሪያ አትከርከሙ፤ ጢማችሁንም አሳጥራችሁ አትቍረጡ።
28“ ‘ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ፤ በሰውነታችሁም ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
29“ ‘ምድሪቱ ወደ ግልሙትና አዘንብላ በርኩሰት እንዳትሞላ፣ ሴት ልጅህ ጋለሞታ ትሆን ዘንድ አታዋርዳት።
30“ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
31“ ‘እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
32“ ‘ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም (ኤሎሂም) ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።
33“ ‘መጻተኛ በምድራችሁ ላይ አብሯችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤ 34አብሯችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብፅ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
35“ ‘በመስፈሪያ ወይም በሚዛን አታጭበርብሩ። 36እውነተኛ መለኪያ፣ እውነተኛ መመዘኛ፣ እውነተኛ የኢፍ#19፥36 ኢፍ የደረቅ ነገር መለኪያ ወይም መስፈሪያ ነው። መስፈሪያ፣ እውነተኛ የኢን#19፥36 ኢን የፈሳሽ ነገር መለኪያ ነው መስፈሪያም ይኑራችሁ። ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) ነኝ።
37“ ‘ሥርዐቴንና ሕጌን ሁሉ ጠብቁ፤ ተከተሏቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ”

Currently Selected:

ዘሌዋውያን 19: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy