YouVersion Logo
Search Icon

ኢሳይያስ 56

56
ለሌሎች የተሰጠ ድነት
1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ፍትሕን ጠብቁ፤
መልካሙን አድርጉ፤
ማዳኔ በቅርብ ነው፤
ጽድቄም ፈጥኖ ይገለጣልና።
2ሰንበትን ሳያረክስ የሚያከብር፣
ክፉን ከማድረግ እጁን የሚሰበስብ፣ የሚገታ፣
እነዚህን የሚፈጽም ሰው የተባረከ ነው።”
3ወደ እግዚአብሔር የተጠጋ መጻተኛ፣
“እግዚአብሔር በርግጥ ከሕዝቡ ይለየኛል” አይበል፤
ጃንደረባም፣
“እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ” አይበል።
4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ሰንበቶቼን ለሚያከብሩ ጃንደረቦች፣
ደስ የሚያሰኘኝን ለሚመርጡ፣
ቃል ኪዳኔን፣ ለሚጠብቁ
5በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣
ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣
መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤
ለዘላለም፣
የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ።
6እርሱን ለማገልገል፣
ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያቈራኙ መጻተኞች፣
የእግዚአብሔርን ስም በመውደድ፣
እርሱንም በማምለክ፣
ሰንበትን ሳያረክሱ የሚያከብሩትን ሁሉ፣
ቃል ኪዳኔንም የሚጠብቁትን፣
7ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤
በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ።
የሚቃጠል መሥዋዕታቸውንና ሌሎች መሥዋዕቶቻቸውን፣
በመሠዊያዬ ቢሠዉ እቀበላቸዋለሁ፤
ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ
የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራልና።”
8የተበተኑትን እስራኤል የሚሰበስብ፣
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ከተሰበሰቡት በተጨማሪ፣
ሌሎችን እንደ ገና እሰበስባለሁ።”
በክፉዎች ላይ የእግዚአብሔር ወቀሣ
9እናንት የምድር አራዊት ሁሉ ኑ፤
እናንት የዱር አራዊት ሁሉ ኑና በጥርሳቸሁ ቦጫጭቁ።
10የእስራኤል ጠባቂዎች ዕውሮች ናቸው፤
ዕውቀት የላቸውም፤
ሁሉም ድምፅ የለሽ ውሾች ናቸው፤
መጮኽ አይችሉም፤
ተጋድመው ያልማሉ፤
እንቅልፋሞች ናቸው።
11እጅግ ሲበዛ ሆዳም ውሾች ናቸው፤
ጠገብሁን አያውቁም፤
የማያስተውሉ እረኞች ናቸው፤
ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ሄዱ፤
እያንዳንዳቸውም የግል ጥቅማቸውን ፈለጉ።
12እርስ በርሳቸውም፣ “ኑና የወይን ጠጅ እንገባበዝ፤
እስክንሰክር እንጠጣ፤
ነገም ያው እንደ ዛሬ፣
ምናልባትም የተሻለ ቀን ይሆንልናል” ይባባላሉ።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 56: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy