YouVersion Logo
Search Icon

ኢሳይያስ 55

55
ጥሪ ለተጠሙ
1እናንት የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤
እናንት ገንዘብ የሌላችሁ፣
ወደ ውሆች ኑ፤
ኑና ግዙ፤ ብሉም፤
ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣
የወይን ጠጅና ወተት ግዙ።
2ገንዘባችሁን እንጀራ ባልሆነ ነገር ላይ ለምን ታጠፋላችሁ?
በማያጠግብስ ነገር ላይ ለምን ጕልበታችሁን ትጨርሳላችሁ?
ስሙ፤ እኔን ስሙኝ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤
ነፍሳችሁም በጥሩ ምግብ ትደሰታለች።
3ጆሯችሁን ከፍታችሁ ወደ እኔ ቅረቡ፤
ነፍሳችሁም እንድትኖር አድምጡኝ።
ለዳዊት በገባሁት በጽኑ ፍቅሬ፣
ከእናንተም ጋር የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።
4እነሆ፤ እርሱን ለሕዝቦች ምስክር፣
መሪ፣ የጦር አዝማችም አድርጌዋለሁ።
5እነሆ፤ የማታውቃቸውን መንግሥታት ትጠራለህ፤
የማያወቁህ መንግሥታት በፍጥነት ወደ አንተ ይመጣሉ፤
ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክህ፣
የእስራኤል ቅዱስ፣
በክብሩ ከፍ ከፍ አድርጎሃል።
6 እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤
ቀርቦም ሳለ ጥሩት።
7ክፉ ሰው መንገዱን፣
በደለኛም ሐሳቡን ይተው።
ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤
ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
8“ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣
መንገዴ እንደ መንገዳችሁ አይደለምና”
ይላል እግዚአብሔር
9“ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣
መንገዴ ከመንገዳችሁ፣
ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።
10ዝናምና በረዶ ከሰማይ ወርዶ፣
ምድርን በማራስ፣
እንድታበቅልና እንድታፈራ
ለዘሪው ዘር፣
ለበላተኛም እንጀራ እንድትሰጥ ሳያደርግ፣
ወደ ላይ እንደማይመለስ ሁሉ፣
11ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣
በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤
ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤
የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።
12በደስታ ትወጣላችሁ፤
በሰላምም ትሸኛላችሁ፤
ተራሮችና ኰረብቶች፣
በፊታችሁ በእልልታ ይዘምራሉ፤
የሜዳ ዛፎች ሁሉ፣
ያጨበጭባሉ።
13በእሾኽ ፈንታ የጥድ ዛፍ፣
በኵርንችት ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል።
ይህም የእግዚአብሔር መታሰቢያ፣
ሊጠፋ የማይችል፣
የዘላለም ምልክት ይሆናል።”

Currently Selected:

ኢሳይያስ 55: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy