YouVersion Logo
Search Icon

ዕብራውያን 2

2
ትኵረት የሚያሻው ጕዳይ
1ስለዚህ ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል። 2ምክንያቱም በመላእክት በኩል የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነና ማንኛውም መተላለፍና አለመታዘዝ ተገቢውን ቅጣት ከተቀበለ፣ 3እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ቸል ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? ይህ ድነት በመጀመሪያ በጌታ ተነገረ፤ ከእርሱ የሰሙትም ለእኛ አረጋገጡልን። 4እግዚአብሔርም በምልክት፣ በድንቅና በልዩ ልዩ ታምራት እንዲሁም እንደ ፈቃዱ በታደሉት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ስለዚሁ ነገር መስክሯል።
ኢየሱስ ወንድሞቹን መሰለ
5ይህን የምንናገርለትን መጪውን ዓለም ለመላእክት አላስገዛም፤ 6ነገር ግን አንዱ በሌላ ስፍራ እንዲህ ብሎ መስክሯል፤
“ታስታውሰው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?
ታስብለትስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው”
7ከመላእክት ጥቂት#2፥7 ወይም ለጥቂት ጊዜ አሳነስኸው፤
የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት፤
8ሁሉንም ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት።
እግዚአብሔር ሁሉን ከበታቹ ሲያስገዛለት፣ ያላስገዛለት ምንም ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ነገር ተገዝቶለት አናይም። 9ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ጥቂት እንዲያንስ ተደርጎ የነበረው ኢየሱስ፣ የሞትን መከራ በመቀበሉ አሁን የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖለት እናየዋለን።
10ሁሉ ነገር ለእርሱና በእርሱ የሚኖር እግዚአብሔር፣ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ለማምጣት፣ የድነታቸውን መሥራች በመከራ ፍጹም ሊያደርገው የተገባ ነበር። 11ሰዎችን የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሰዎች ከአንድ ቤተ ሰብ ናቸው፤ ስለዚህ ኢየሱስ ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም፤ 12እንዲህም ይላል፤
“ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤
በጉባኤም መካከል ምስጋናህን እዘምራለሁ።”
13እንዲሁም፣
“እኔ በእርሱ እታመናለሁ።”
ደግሞም እንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች።”
14ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ፣ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ 15እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው። 16እርሱ የመጣው መላእክትን ለመርዳት ሳይሆን፣ የአብርሃምን ዘር ለመርዳት እንደ ሆነ ግልጽ ነው። 17ስለዚህ በሁሉም ነገር ወንድሞቹን መምሰል ተገባው፤ ይህንም ያደረገው መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለሕዝቡ የኀጢአትን ስርየት ለማስገኘት#2፥17 የእግዚአብሔርን ቍጣ ለመመለስ ነው። 18እርሱ ራሱ በተፈተነ ጊዜ መከራን ስለ ተቀበለ፣ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።

Currently Selected:

ዕብራውያን 2: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy