መጽሐፈ ሲራክ 36
36
ስለ እስራኤል ደኀንነትና መታደስ የቀረበ ጸሎት
1የዓለም ጌታ አምላክ ሆይ፥ ወደ እኛ ተመልከት፥ ራራልን፤ ሌሎች ሕዝቦችም ይፈሩህ ዘንድ አድርግ። 2በአገሮች ላይ ሁሉ እጅህን አንሣ፤ ኃያልነትህንም አሳያቸው። 3በእነርሱ ፊት ለእኛ ቅድስነትህን እንዳሳየኸን ሁሉ፥ አሁን ደግሞ በእኛ ፊት ታላቅነትህን ለእነርሱ አሳያቸው። 4እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! ካንተ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እኛ እንዳወቅን፥ እነርሱም ያውቁህ ዘንድ አድርግ። 5አዳዲስ ምልክቶችን ላክ፤ ታምራቶችንም ሥራ፤ ለእጅህና ለቀኝ ክንድህ ክብርን ስጥ። 6ቁጣህን አምጣ፤ መዓትህን አውርድ፤ ተቃዋሚህን አጥፋ፤ ጠላትህንም ደምስስ። 7ቀኑን አፍጥን፤ የገባኸውን ቃል አስታውስ፤ ስለ አስደንጋጭ ሥራህም ይነገር። 8ቀሪዎቹን ሰዎች ነበልባላዊ ቁጣህ ይብላቸው፤ ሕዝብህን የጨቆኑ ይደምሰሱ። 9የጨካኝ መሪዎችን፥ ከእኛ ሌላ ማንም የለም! የሚሉትን ሁሉ፥ ጭንቅላታቸውን አፍርስ። 10የያዕቆብን ነገዶች አሰባስብ፤ እንደ መጀመሪያው ጊዜም ርስታቸውን መልሰህ ስጣቸው። 11ጌታ ሆይ! በስምህ ለሚጠራው የክብር ልጅህ ለሆነው ለእስራኤል ራራለት። 12ለቅድስት ከተማህ፥ ማረፊያህ ለሆነችው ለኢየሩሳሌም ርኀራኄ ይኑርህ። 13ጽዮንን በምስጋናህ፥ ቤተ መቅደስህን በክብርህ ሙላት። 14በመጀመሪያ የፈጠርኻቸውን አንጻቸው፤ በስምህ የተተነበየውን ሁሉ ፈጽም። 15አንተን ለሚጠብቁህ ሁሉ ሽልማታቸውን ስጥ፤ ነቢዮችህም ትክክለኞች እንደ ነበሩ አረጋግጥ። 16ጌታ ሆይ! የአሮንን ምርቃት እንደተቀበልህ፥ የአገልጋዮችህንም ጸሎት እንዲሁ ተቀበል። 17በዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎችም ሁሉ፥ ጌትነትህንና ዘላለማዊ አምላክነትህን ይቀበላሉ።
መለየት
18ሆዳችን ሁሉንም ዓይነት መብል ይቀበላል፤ አንዳንዶቹ ግን ከሌሎቹ የተሻሉ ናቸው። 19ምላስ የሥጋን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፥ አስተዋል አድማጭም የውሸት ቃልን ይለያል። 20ተንኮለኛ ሰው ሌሎችን ያሳዝናል፤ እንዲህ ዓይነቱን ለመቀበል ልምድ ያሻል።
ሚስት መምረጥ
21ሴት የመጣላትን ባል ትቀበላለች፤ አንዳንድ ሴት ልጆች ግን ከሌሎች የተሻሉ ናቸው። 22የሴት ልጅ ውበት ተመልካቹን ያስደስታል፤ ወንድ ከዚህ የተሻለ የሚወደው ነገር የለም። 23ምላሷ ደግና ልስልስ ከሆነ፥ ባሏ ከወንዶች ሁሉ ደስተኛ ነው። 24ሚስት የሚያገባ ሰው ወደ መልካም ዕድል መንገዱን አቅንቷል፤ እርሱን የምትመስል ረዳትና ደጋፊ ምሰሶም አፍርቷል። 25ንብረት ያለ አጥር የዘራፊ ሲሳይ ነው፤ ሚስት የሌለውም ወንድ እንዲሁ ዓላማ ቢስና ብስጩ ይሆናል። 26ከተማ ለከተማ የሚራወጠውንና የታጠቀውን ሌባ የሚያምን ይኖራልን? 27ጐጆ የሌለውና በመሸበት የሚያድርም ሰው እንዲሁ ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 36: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in