መጽሐፈ ሲራክ 29
29
ብድር
1 #
ዘፀ. 22፥25፤ ዘሌ. 25፥35-38። ለባልጀራህ ማበደር የምሕረት ሥራ ነው፤ የዕርዳታ እጅህን መዘርጋት፤ ትእዛዛቱን ማክበር ነው። 2ባልንጀራህ ሲቸገር አበድረው፤ አንተም ብድርህን በወቅቱ መልስለት። 3ቃልህን አክብር፤ ለእርሱ ታማኝ ሁን፤ ሁልጊዜም የሚያስፈልግህን ታገኛለህ። 4ብዙዎች ብድርን ንፋስ እንደጣለው ፍሬ ይቆጥሩታል፤ በችግራቸውም ጊዜ የደረሱላቸውን ሰዎች ያስቀይማሉ። 5ሰው የሚፈልገውን እስኪያገኝ የባልንጀራውን እጅ ይስማል፤ ስለ አበዳሪውም ሀብት በትሕትና ይናገራል። የመክፈያው ጊዜ ሲደርስ ግን ቀኑን ያስተላልፋል፤ እንዳመጣለት ይናገራል፤ ጊዜውም እንዲራዘምለት ይጠይቃል። 6እንዲከፍል ቢገደድ እንኳ አበዳሪው ግማሹን ብቻ ቢያገኝ ነው፤ ያንንም እንደ ትልቅ ዕድል ይቆጥረዋል። ካልሆነ ግን ገንዘቡን ተነጥቆ በራሱም ላይ ጠላትን ያፈራል። ወሮታውም፥ እርግማንና ውርደት በክብርም ፈንታ ስድብ ይሆናል። 7ብዙዎች ለማበደር አይፈቅዱም፤ ከልብ ክፋት የመነጨ አይደለም፤ ገንዘባቸውን ላለማስነጠቅ ሲሉ እንጂ።
ምጽዋት
8ለድሆች ግን ለጋስ ሁን፤ ቸርነትህን ያገኙም ዘንድ አታስጠብቃቸው፤ 9ትእዛዙን በማክበር ችግረኞችን እርዳ፤ በመከራም ጊዜ ባዶ እጃቸውን አትሸኛቸው። 10ወንድምህን ወይም ወዳጅህን በገንዘብህ እርዳ፤ ብትቀብረውም ይበሰብሳልና። 11ልዑል እግዚአብሔር እንዳዘዘው በሀብትህ ተጠቀም፤ ትእዛዙን መፈጸምህ ከወርቅ የተሻለ ትርፍ ይሆንልሃል። 12ጐተራዎችህን በምጽዋት ሙላ፤ ምግባርህም ከአደጋ ሁሉ ይሰውርሃል። 13ከጠንካራ ጋሻ፥ ከከባድ ጦርም ይልቅ፥ ከጠላቶችህ ጋር ይዋጋልሃል።
ዋስትናዎች
14ደግ ሰው ባለእንጀራውን ይዋሳል፤ ዕረፍተ ቢስ ሰው ግን ጥሎት ይሄዳል። 15ዋስህ የዋለልህን ውለታ አትርሳ፤ ላንተ ሲል ሕይወቱን ሰጥቷል። 16ኃጢአተኛ ስለ ዋሱ ደኀንነት አያስብም፤ ምስጋና ቢሱ አዳኙን ይረሳል፤ 17ዋስትና ብዙ ባለጸጐችን አክስሯል፤ በባሕር ማዕበልም ውስጥ ጥሏቸዋል። 18ኃያላኑን ከቤታቸው አባርሯል፤ በባሕር ማዕበልም ውስጥ ጥሏቸዋል። 19ለትርፍ ሲል ዋስ ለመሆን የሚፈጥን፥ ፍርድን ለመቀበል ይጣደፋል። 20ባልንጀራህን እንደ አቅምህ እርዳ፤ እንደ እርሱ ችግር ላይ እንዳትወድቅ ግን ተጠንቀቅ። 21ለሕይወት የሚያሰፈልጉ ዋነኛ ነገሮች፥ ሙያ፥ እንጀራና ልብስ ናቸው፤ የግል ኑሮን ለመምራት ደግሞ መጠለያ ያስፈልጋል። 22በሌላ ሰው ቤት ደልቶህ ከመኖር፥ በደሳሳ ጐጆህ ውስጥ ሕይወትህን መምራት ይሻላል። 23ብዙም ይኑርህ ጥቂት ባለህ ተደሰት፤ ከቤተሰቦችህም ምሬት አትሰማም። 24ከቤት እቤት መቀየር አስቸጋሪ ሕይወት ነው። የትም ብትሄድ ለመናገር አትደፍርም። 25የእነርሱ አይደለህም፤ ለምትቀዳው መጠጥ አትመሰገንም፤ ንግግራቸውም ያንገበግብሃል። 26ና ወዲህ አንተ ባይተዋር ማዕድ አዘጋጅ፤ ምን ይኖርሃል? የሚበላ ነገር ስጠኝ! 27ባይተዋር ቦታ ፈልግ፤ ታላቅ እንግዳ መጥቶብኛል፤ ወንድሜ ከእኔ ዘንድ ያርፋል፤ ቤቱን እፈልገዋለሁ፤ ትባላለህ። 28እንደ እንግዳ አለመስተናገድ፥ እንደ ባለዕዳ ውርደትን መቀበል፥ ለአዋቂ ሰው እጅጉን ይከብዳል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 29: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in