YouVersion Logo
Search Icon

ዘካርያስ 14

14
እግዚአብሔር ይመጣል፤ ይነግሣልም
1እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፤ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ።
2ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዪቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማዪቱ እኩሌታ ይማረካል፤ የሚቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዪቱ አይወሰድም።
3 እግዚአብሔርም በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል። 4በዚያን ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤ 5እናንተም በእግዚአብሔር ተራራ ሸለቆ በኩል በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር ትሸሻላችሁ፤ ሸለቆው እስከ አጸል ይደርሳልና። በምድር መናወጥ#14፥5 ወይም ተራራዬ ሸለቆ ይሮጣል፤ እስከ አጸል ይስፋፋል። በርዕደ መሬት ሳቢያ እንደ ተዘጋው ሁሉ ለወደፊቱም እንደዚያ ይሆናል ምክንያት ሸሽታችሁ እንደ ነበረ ትሸሻላችሁ፤ ከዚያም አምላኬ እግዚአብሔር ይመጣል፤ ቅዱሳኑም ሁሉ አብረውት ይመጣሉ።
6በዚያ ቀን በረዶ ውርጭና ብርሃን አይኖርም። 7ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።
8በዚያን ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር#14፥8 ሙት ባሕር ነው።፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር#14፥8 ሜድትራኒያን ነው። ይፈስሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል።
9 እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር አንድ፣ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል።
10ምድር ሁሉ ከጌባ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሬሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች። 11የሰው መኖሪያም ትሆናለች፤ ከቶም ዳግመኛ አትፈርስም፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት በሰላም ትኖራለች። 12እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጕድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ። 13በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል። 14ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል። 15ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችን፣ በቅሎዎችን ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሶች ሁሉ ይመታል።
16ከዚያም ኢየሩሳሌምን ከወጓት አሕዛብ ከሞት የተረፉት ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ለመስገድና የዳስን በዓል ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ። 17የምድር ሕዝብ ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ከሆነ ዝናብ አያገኙም። 18የግብፅም ሰዎች ወደዚያ ሳይወጡ ቢቀሩ፣ ዝናብ አያገኙም፤ እግዚአብሔር ወጥተው የዳስ በዓልን በማያከብሩ አሕዛብ ላይ የሚያደርሰውን መቅሠፍት በእነርሱም ላይ ያመጣል። 19የዳስን በዓል ወጥተው ለማያከብሩ ግብፃውያንና አሕዛብ ሁሉ የተወሰነው ቅጣት ይህ ነው።
20በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር” የሚል ጽሑፍ ይቀረጻል፤ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ የማብሰያ ምንቸቶች ከመሠዊያው ፊት ለፊት እንዳሉ ሳሕኖች የተቀደሱ ይሆናሉ። 21በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸባኦት የተቀደሱ ይሆናሉ፤ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚመጡ ሁሉ ምንቸቶቹን በመውሰድ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያን ቀን በእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ከነዓናዊ#14፥21 ወይም ነጋዴ እነዚህ ሕዝቦች በአብዛኛው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሳይሆኑ አይቀሩም። አይገኝም።

Currently Selected:

ዘካርያስ 14: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy