YouVersion Logo
Search Icon

ሮሜ 14

14
በወንድምህ ላይ አትፍረድ
1በእምነቱ ደካማ የሆነውን ሰው፣ አከራካሪ በሆኑ ጕዳዮች ላይ በአቋሙ ሳትፈርዱበት ተቀበሉት። 2የአንድ ሰው እምነቱ ማንኛውንም ነገር እንዲበላ ይፈቅድለታል፤ በእምነቱ ያልጠነከረው ሌላው ሰው ግን አትክልት ብቻ ይበላል። 3ማንኛውንም የሚበላ የማይበላውን አይናቅ፤ የማይበላውም፣ የሚበላውን አይኰንን፤ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። 4ሌላውን በሚያገለግል ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ? እርሱ ቢወድቅ ወይም ቢቆም ለጌታው ነው፤ ጌታ ሊያቆመው ስለሚችልም ይቆማል።
5አንድ ሰው አንዱን ቀን ከሌላው የተሻለ ቅዱስ አድርጎ ይቈጥራል፤ ሌላው ደግሞ ቀኖች ሁሉ እኩል እንደ ሆኑ ያስባል። እያንዳንዱ የራሱን ውሳኔ ልብ ብሎ ይወስን። 6አንድን ቀን ከሌላው የተለየ አድርጎ የሚያስብ ሰው፣ እንዲህ የሚያደርገው ለጌታ ብሎ ነው፤ ሥጋ የሚበላውም ለጌታ ብሎ ይበላል፤ ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባልና። የማይበላም ለጌታ ሲል አይበላም፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ያቀርባል። 7ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና። 8ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን።
9ለዚሁ፣ የሙታንና የሕያዋን ጌታ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ሞቷል፤ በሕይወትም ተነሥቷል። 10ታዲያ አንተ በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ? ለምንስ ወንድምህን ትንቃለህ? ሁላችንም በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ 11እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤
“ ‘እኔ ሕያው ነኝና’፤
‘ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤
ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር ይመሰክራል’ ”
ይላል ጌታ። 12ስለዚህ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።
13ስለዚህ እርስ በርሳችን፣ አንዱ በሌላው ላይ ከመፍረድ እንቈጠብ፤ በዚህ ፈንታ ግን በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቍርጥ ሐሳብ አድርግ። 14በጌታ በኢየሱስ ሆኜ በራሱ ንጹሕ ያልሆነ ምንም ምግብ#14፥14 ወይም ምንም ነገር እንደሌለ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን አንድ ሰው አንድን ነገር ንጹሕ እንዳልሆነ የሚቈጥር ከሆነ፣ ያ ነገር ለእርሱ ንጹሕ አይደለም። 15ወንድምህ በምትበላው ምግብ የሚያዝን ከሆነ፣ በፍቅር አልተመላለስህም፤ ክርስቶስ የሞተለትን ወንድምህን በመብልህ አታጥፋው። 16መልካም ነው ብለህ የምታስበው ነገር ክፉ ተብሎ እንዲነቀፍ አታድርግ። 17የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም፣ በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ሐሤት ነው እንጂ፣ የመብልና የመጠጥ ጕዳይ አይደለም፤ 18በዚህ ሁኔታ ክርስቶስን የሚያገለግል እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፤ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው።
19ስለዚህ ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ። 20ለምግብ ስትል የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ለሌላው ሰው የመሰናከያ ምክንያት የሚሆነውን መብላት ስሕተት ነው። 21ለወንድምህ መሰናከል ምክንያት የሚሆነውን ሥጋን አለመብላት፣ ወይንን አለመጠጣት፣ ወይም አንዳች ነገርን አለማድረግ መልካም ነው።
22እንግዲያስ ስለ እነዚህ ነገሮች ያለህ እምነት በአንተና በእግዚአብሔር መካከል የተጠበቀ ይሁን፤ ትክክል ነው ብሎ በተቀበለው ነገር ራሱን የማይኰንን የተባረከ ሰው ነው። 23ነገር ግን የሚጠራጠር ሰው ቢበላ በእምነት ስላልሆነ፣ ተፈርዶበታል፤ በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነውና።

Currently Selected:

ሮሜ 14: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy