YouVersion Logo
Search Icon

ማቴዎስ 5

5
የተራራው ስብከት
5፥3-12 ተጓ ምብ – ሉቃ 6፥20-23
1ብዙ ሕዝብ እንደ ተሰበሰበ ባየ ጊዜ፣ ወደ ተራራ ወጣና ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ መጡ። 2እንዲህም እያለ ያስተምራቸው ጀመር፤
3 “በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤
መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና።
4 የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤
መጽናናትን ያገኛሉና።
5 የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤
ምድርን ይወርሳሉና።
6 ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤
ይጠግባሉና።
7 ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤
ምሕረትን ያገኛሉና።
8 ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤
እግዚአብሔርን ያዩታልና።
9 ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና።
10 ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤
መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና።
11 “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። 12በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳድደዋቸዋልና።
ጨውና ብርሃን
13 “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላልን? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ጥቅም አይኖረውም።
14 “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤ 15ሰዎችም መብራት አብርተው ከዕንቅብ ሥር አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ። 16እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።
የሕግ ፍጻሜ
17 “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። 18እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም። 19ስለዚህ ማንም ከእነዚህ ትእዛዞች አነስተኛዪቱን እንኳ ቢተላለፍ፣ ሌሎችንም እንዲተላለፉ ቢያስተምር፣ በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዞች እየፈጸመ ሌሎችም እንዲፈጽሙ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይባላል። 20ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም።
ነፍስ መግደል አይገባም
5፥2526 ተጓ ምብ – ሉቃ 12፥5859
21 “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ 22እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል።
23 “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፣ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ 24መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።
25 “የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ በወህኒም እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ። 26እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም#5፥26 ግሪኩ ኮድራንቴስ ይላል። እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም።
ማመንዘር አይገባም
27 “ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 28እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዐይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሯል። 29ቀኝ ዐይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። 30ቀኝ እጅህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል።
31 “ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት መስጠት አለበት’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 32እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በላዩ ላይ ስታመነዝር ካላገኛት በስተቀር፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውን ሴት ያገባም እንዳመነዘረ ይቈጠራል።
ስለ መሐላ
33 “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘በሐሰት አትማል፤ በእግዚአብሔር ፊት የማልኸውንም ጠብቅ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 34እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ 35በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና 36በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከጠጕራችሁ መካከል አንዲቷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና። 37ስለዚህ ስትነጋገሩ ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ፣ ‘አዎን’፤ አይደለም፣ ከሆነ ‘አይደለም’ ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው የሚመጣ ነውና።
ስለ መበቀል
38 “ ‘ዐይን ስለ ዐይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 39እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት’፤ ነገር ግን ቀኝ ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጕንጭህን ደግሞ አዙርለት። 40አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው። 41አንድ ሰው አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ። 42ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚሻውን ፊት አትንሣው።
43 “ ‘ወዳጅህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 44እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤#5፥44 አንዳንድ የጥንት ቅጆች የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ ይላሉ። ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ። 45እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል። 46የሚወድዷችሁን ብቻ የምትወድዱ ከሆነ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ? ቀራጮችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? 47ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ የምትነሡ ከሆነ ከሌሎች በምን ትሻላላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? 48ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።

Currently Selected:

ማቴዎስ 5: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy