YouVersion Logo
Search Icon

ማቴዎስ 23

23
ኢየሱስ ፈሪሳውያንንና የኦሪት ሕግ መምህራንን ነቀፈ
23፥1-7 ተጓ ምብ – ማር 12፥3839ሉቃ 20፥45-46
23፥37-39 ተጓ ምብ – ሉቃ 13፥3435
1ከዚያም ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ 2“የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል። 3ስለዚህ የሚነግሯችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እንደሚናገሩት አያደርጉምና ተግባራቸውን አትከተሉ። 4እንዲሁም ለመሸከም የማይቻል ከባድ ሸክም አስረው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ ራሳቸው ግን በጣታቸው እንኳ አይነኩትም።
5 “ለመታየት ሲሉ የሚያደርጉትን ሁሉ በሰው ፊት ያደርጋሉ፤ አሸንክታባቸውን # 23፥5 ከቅዱሳት መጻሕፍት የተወሰዱ ጥቅሶች የተጻፉበት በግንባርና በክንድ ላይ የሚታሰር ትንሽ ጥቅልል ነው። ያሰፋሉ፤ የቀሚሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ። 6በግብዣ ቦታ የከበሬታ ስፍራ፣ በምኵራብም የመጀመሪያውን መቀመጫ መያዝ ይወድዳሉ። 7እንዲሁም በገበያ መካከል ሰላምታ መቀበልንና በሰዎች አንደበት ‘መምህር’ ተብለው መጠራትን ይሻሉ።
8 “እናንተ ግን ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ፤ አስተማሪያችሁ አንድ ብቻ ነው፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁና። 9በሰማይ ያለ አንድ አባት ስላላችሁ፣ በምድር ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ። 10መምህራችሁ አንዱ ክርስቶስ ስለሆነ፣ ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ። 11ከመካከላችሁ ከሁላችሁ የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል፤ 12ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፣ ራሱን የሚያዋርድ ግን ይከበራል።
13 “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገቡ በሰዎች ላይ በሩን ስለምትዘጉባቸው ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ መግባት የሚፈልጉትንም አታስገቡም። 14እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ የመበለቶችን ቤት እያራቈታችሁ፣ ለሰው ይምሰል ረዥም ጸሎት ስለምታደርጉ የከፋ ፍርድ ትቀበላላችሁ።#23፥14 አንዳንድ ትርጕሞች ይህን ክፍል አይጨምሩም።
15 “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ አንድን ሰው ወደ አይሁድ ሃይማኖት ለማስገባት በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙ፣ ባመነም ጊዜ ከእናንተ በዕጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት ወዮላችሁ።
16 “እናንተ ዕውር መሪዎች፤ ወዮላችሁ! ‘ማንም በቤተ መቅደስ ቢምል ምንም አይደለም፤ ነገር ግን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል መሐላው ይደርስበታል’ ትላላችሁ። 17እናንተ የታወራችሁ ተላላዎች! ከወርቁና ወርቁን ከቀደሰው ቤተ መቅደስ የቱ ይበልጣል? 18እንዲሁም፣ ‘ማንም በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ ነገር ግን በላዩ ላይ ባለው መባ ቢምል መሐላው ይደርስበታል’ ትላላችሁ፤ 19እናንተ ዕውሮች፤ ከመባውና መባውን ከቀደሰው መሠዊያ የቱ ይበልጣል? 20ስለዚህ፣ በመሠዊያው የማለ፣ በመሠዊያውና በላዩ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል። 21እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የማለ፣ በቤተ መቅደሱና በውስጡ በሚያድረው ይምላል። 22በሰማይ የማለም በእግዚአብሔር ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ይምላል።
23 “እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር፤ 24እናንት የታወራችሁ መሪዎች፤ ትንኝን አጥርታችሁ ትጥላላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ።
25 “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ትወለውላላችሁ፤ በውስጣቸው ግን ቅሚያና ሥሥት ሞልቶባቸዋል። 26አንተ ዕውር ፈሪሳዊ አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጥ አጽዳ፤ ከዚያም ውጭው የጸዳ ይሆናል።
27 “እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ውጫቸው በኖራ ተለስነው የሚያምሩ፣ ውስጣቸው ግን በሙታን ዐፅምና በብዙ ርኩሰት የተሞላ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ! 28እናንተም በውጭ ለሰዎች ጻድቃን ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በክፋት የተሞላ ነው።
29 “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር እየገነባችሁ፣ የጻድቃንንም ሐውልት እያስጌጣችሁ፣ 30‘በአባቶቻችን ዘመን ብንኖር ኖሮ፣ የነቢያትን ደም በማፍሰስ አንተባበራቸውም ነበር’ ትላላችሁና። 31በዚህም የነቢያት ገዳዮች ለነበሩት አባቶቻችሁ ልጆች መሆናችሁን በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። 32እንግዲህ የአባቶቻችሁን ጅምር ተግባር ከፍጻሜ አድርሱ!
33 “እናንተ እባቦች፤ የእፉኝት ልጆች! ከገሃነም ፍርድ እንዴት ልታመልጡ ትችላላችሁ? 34ስለዚህ ነቢያትን፣ ጠቢባንንና መምህራንን እልክላችኋለሁ፤ ከነዚህም አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ትሰቅላላችሁ፤ ሌሎቹንም በምኵራቦቻችሁ ትገርፏቸዋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ታሳድዷቸዋላችሁ። 35ስለዚህ፣ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በመቅደሱና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፣ በምድር ላይ ለፈሰሰው ንጹሕ ደም ሁሉ እናንተ ተጠያቂዎች ናችሁ። 36እውነት እላችኋለሁ፤ ላለፈው ነገር ሁሉ ይህ ትውልድ ይጠየቅበታል።
37 “አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ አንቺ ኢየሩሳሌም! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ! እናንተ ግን ፈቃደኛ አልሆናችሁም፤ 38እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀርላችኋል! 39እላችኋለሁና፤ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስከምትሉ ድረስ ዳግመኛ አታዩኝም።”

Currently Selected:

ማቴዎስ 23: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy