YouVersion Logo
Search Icon

ሉቃስ 1

1
መግቢያ
1፥1-4 ተጓ ምብ – ሐሥ 1፥1
1በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት#1፥1 በርግጥ ስለ ታመኑት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያህል ጽፈውት ይገኛል፤ 2ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላለፉልን ነው። 3ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፤ እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ፤ 4ይህንም የማደርገው የተማርኸው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው።
የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ
5በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን፣ ከአብያ የክህነት ምድብ የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ ሚስቱ ኤልሳቤጥም ከአሮን ነገድ ነበረች። 6ሁለቱም የጌታን ትእዛዝና ሥርዐት ሁሉ ጠብቀው ያለ ነቀፋ የሚኖሩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ 7ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መካን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ።
8አንድ ቀን ዘካርያስ በምድቡ ተራ፣ በእግዚአብሔር ፊት በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ፣ 9በሥርዐተ ክህነቱ መሠረት፣ ወደ ጌታ ቤተ መቅደስ ገብቶ ለማጠን በዕጣ ተመረጠ። 10ዕጣን በሚታጠንበትም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆኖ ይጸልይ ነበር።
11የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው። 12ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። 13መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። 14በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤ 15በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ በእናቱም ማሕፀን ሳለ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል። 16ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ 17የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።”
18ዘካርያስም መልአኩን፣ “ይህን በምን ዐውቃለሁ? እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜ ገፍታለች” አለው።
19መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህን እነግርህና ይህን የምሥራች አመጣልህ ዘንድ ተልኬአለሁ፤ 20እነሆ፤ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፣ ይህም እስከሚፈጸምበት ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም።”
21በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ዘካርያስ ከቤተ መቅደሱ ሳይወጣ ለምን እንደ ዘገየ በመገረም ይጠባበቅ ነበር። 22ከወጣ በኋላም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ በምልክት ከመጥቀስ በስተቀር መናገር ባለ መቻሉ በቤተ መቅደስ ውስጥ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ።
23ዘካርያስም የአገልግሎቱ ወቅት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ተመለሰ። 24ከዚህ በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ አምስት ወራትም ራሷን ሰወረች፤ 25እርሷም፣ “ጌታ በምሕረቱ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ሊያስወግድልኝ ተመልክቶ በዚህ ጊዜ ይህን አድርጎልኛል” አለች።
የኢየሱስ መወለድ አስቀድሞ ተነገረ
26በስድስተኛው ወር፣ እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ናዝሬት ከተማ ላከው፤ 27የተላከውም ከዳዊት ዘር ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ነበር፤ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። 28መልአኩም እርሷ ወዳለችበት ገብቶ፣ “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፤ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ የተባረክሽ ነሽ” አላት።
29ማርያምም በንግግሩ እጅግ በጣም ደንግጣ፣ “ይህ ምን ዐይነት ሰላምታ ይሆን?” እያለች ነገሩን ታሰላስል ጀመር፤ 30መልአኩም እንዲህ አላት፤ “ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ። 31እነሆ፤ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። 32እርሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑል ልጅም ይባላል፤ ጌታ አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ 33በያዕቆብም ቤት ላይ ለዘላለም ይነግሣል፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።”
34ማርያምም መልአኩን፣ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው።
35መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፤ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። 36እነሆ፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተ እርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መካን የተባለችውም ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ 37ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”
38ማርያምም፣ “እነሆ፤ እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ።
ማርያም ኤልሳቤጥን ጥየቃ ሄደች
39ማርያምም በዚያው ሰሞን በፍጥነት ተነሥታ ወደ ደጋው አገር፣ ወደ አንድ የይሁዳ ከተማ ሄደች፤ 40ወደ ዘካርያስ ቤትም ገብታ ለኤልሳቤጥ ሰላምታ አቀረበች። 41ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፣ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ 42ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፤ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። 43ለመሆኑ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እኔ ማን ነኝ? 44እነሆ፤ የሰላምታሽ ድምፅ ጆሮዬ እንደ ገባ፣ በማሕፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። 45ጌታ ይፈጸማል ብሎ የነገራትን ያመነች እርሷ የተባረከች ናት!”
የማርያም መዝሙር
46ማርያምም እንዲህ አለች፤
“ነፍሴ ጌታን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤
47መንፈሴም በመድኀኒቴ በእግዚአብሔር ደስ ትሰኛለች፤
48እርሱ የባሪያውን መዋረድ ተመልክቷልና።
ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ
ብፅዕት ይሉኛል፤
49ኀያል የሆነው እርሱ ታላቅ
ነገር አድርጎልኛልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤
50ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ
እስከ ትውልድ ይኖራል።
51በክንዱ ብርቱ ሥራ ሠርቷል፤
በልባቸው ሐሳብ የሚታበዩትን በትኗቸዋል፤
52ገዦችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል፤
ትሑታንን ግን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል፤
53የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቧቸዋል፤
ሀብታሞችን ግን ባዷቸውን ሰድዷቸዋል፤
54ምሕረቱን በማስታወስ፣ ባሪያውን
እስራኤልን ረድቷል፤
55ይህም ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፣
ለአብርሃምና ለዘሩ ያለውን ለዘላለም ለመጠበቅ ነው።”
56ማርያምም ሦስት ወር ያህል ኤልሳቤጥ ዘንድ ከቈየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።
የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ
57የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። 58ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ጌታ ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰሙ፤ የደስታዋም ተካፋዮች ሆኑ።
59በስምንተኛውም ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤ በአባቱም ስም ዘካርያስ ሊሉት ፈለጉ፤ 60እናቱ ግን፣ “አይሆንም፤ ዮሐንስ መባል አለበት” አለች።
61እነርሱም፣ “ከዘመዶችሽ በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት።
62አባቱንም ምን ስም ሊያወጣለት እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። 63እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ፤ ሁሉም በነገሩ ተደነቁ። 64ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱ ተፈታ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ መናገር ጀመረ። 65ጎረቤቶቹም ሁሉ በፍርሀት ተሞሉ፤ ይህም ሁሉ ነገር በደጋማው የይሁዳ ምድር ሁሉ ተወራ። 66ይህንም የሰሙ ሁሉ፣ “ይህ ሕፃን ምን ሊሆን ይሆን?” እያሉ ነገሩን በልባቸው ያዙ፤ የጌታ እጅ በርግጥ ከእርሱ ጋር ነበርና።
የዘካርያስ ትንቢት
67የሕፃኑም አባት ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤
68“የእስራኤል አምላክ፣ ጌታ ይመስገን፤
መጥቶ ሕዝቡን ተቤዥቷልና።
69በባሪያው በዳዊት ቤት፣
የድነት ቀንድ#1፥69 ቀንድ በዚህ ስፍራ ብርታትን በትእምርትነት ያሳያል። አስነሥቶልናል፤
70ይህም ጥንት በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው፣
71ማዳኑም ከጠላቶቻችንና፣
ከተፃራሪዎቻችን ሁሉ እጅ ነው፤
72ይህንም ያደረገው ለአባቶቻችን ምሕረቱን ለማሳየት፣
ቅዱስ ኪዳኑን ለማስታወስ፣
73ለአባታችን ለአብርሃም የማለውን መሐላ ለማሰብ፣
74ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶ፣
ያለ ፍርሀት እንድናገለግለው፣
75በዘመናችንም ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ ሊያቆመን ነው።
76“ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፤ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤
የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት በፊቱ ትሄዳለህና፤
77የኀጢአታቸውን ስርየት ከማግኘታቸው የተነሣ፤
ለሕዝቡ የመዳንን ዕውቀት ትሰጥ ዘንድ፣
78ከአምላካችንም በጎ ምሕረት የተነሣ፣
የንጋት ፀሓይ ከሰማይ ወጣችልን፤
79ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣
በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራና፣
እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ ነው።”
80ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም ሕዝብ በይፋ እስከ ታየበት ቀን ድረስ በበረሓ ኖረ።

Currently Selected:

ሉቃስ 1: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy