YouVersion Logo
Search Icon

ኢዩኤል 2

2
የአንበጣ ሰራዊት
1በጽዮን መለከትን ንፉ፤
በቅዱሱ ተራራዬም የማስጠንቀቂያውን ድምፅ አሰሙ።
በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤
የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና፤
እርሱም በደጅ ነው።
2ይህም የጨለማና የጭጋግ ቀን፣
የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው።
የንጋት ብርሃን በተራሮች ላይ እንደሚወጣ፣
ኀያልና ብዙ ሰራዊት ይመጣል፤
ከጥንት እንዲህ ዐይነት ከቶ አልነበረም፤
በሚመጡትም ዘመናት እንዲህ ዐይነት ከቶ አይሆንም።
3በፊታቸው፣ እሳት ይባላል፤
በኋላቸውም ነበልባል ይለበልባል፤
በፊታቸው ምድሪቱ እንደ ዔድን ገነት ናት፤
በኋላቸውም የሚቀረው ባዶ ምድረ በዳ ነው፤
ምንም አያመልጣቸውም።
4መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፤
እንደ ጦር ፈረስም ይጋልባሉ።
5ገለባ እንደሚበላ እንደሚንጣጣ እሳት፣
ለጦርነት እንደ ተዘጋጀ ኀያል ሰራዊት፣
የሠረገሎችን ድምፅ የሚመስል ድምፅ እያሰሙ፣
በተራሮች ጫፍ ላይ ይዘልላሉ።
6በእነርሱ ፊት ሕዝቦች ይርዳሉ፤
የሁሉም ፊት ይገረጣል።
7እንደ ተዋጊዎች ድንገት አደጋ ይጥላሉ፤
እንደ ወታደሮችም ቅጥርን ይዘልላሉ፤
ከመንገዳቸውም ሳይወጡ፣
አቅጣጫ ይዘው ይጓዛሉ።
8እርስ በርሳቸው አይገፋፉም፤
እያንዳንዱ መሥመሩን ጠብቆ ይሄዳል፤
መሥመራቸውን ሳይለቁ፣
መከላከያውን ሰብረው ያልፋሉ።
9ከተማዪቱን ይወርራሉ፤
በቅጥሩም ላይ ይዘልላሉ፤
በቤቶች ላይ ዘልለው ይወጣሉ፤
እንደ ሌባም በመስኮት ይገባሉ።
10ምድር በፊታቸው ትንቀጠቀጣለች፤
ሰማይም ይናወጣል፤
ፀሓይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤
ከዋክብትም ከእንግዲህ ወዲያ አያበሩም።
11በሰራዊቱ ፊት፣
እግዚአብሔር ያንጐደጕዳል፤
የሰራዊቱ ብዛት ስፍር ቍጥር የለውም፤
ትእዛዙንም የሚያደርግ እርሱ ኀያል ነው፤
የእግዚአብሔር ቀን ታላቅ፣
እጅግም የሚያስፈራ ነው፤
ማንስ ሊቋቋመው ይችላል?
ልባችሁን ቅደዱ
12“አሁንም ቢሆን፣
በጾም፣ በልቅሶና በሐዘን፣
በፍጹም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ” ይላል እግዚአብሔር
13ልባችሁን እንጂ፣
ልብሳችሁን አትቅደዱ፤
ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤
እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ፣
ቍጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ፣
ክፉ ነገር ከማምጣትም የሚታገሥ ነውና።
14በምሕረቱ ተመልሶ፣
ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የሚሆነውን፣
የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን እንዲተርፋችሁ፣
በረከቱን ይሰጣችሁ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?
15በጽዮን መለከትን ንፉ፤
ቅዱስ ጾምን ዐውጁ፤
የተቀደሰን ጉባኤ ጥሩ።
16ሕዝቡን ሰብስቡ፤
ጉባኤውን ቀድሱ፤
ሽማግሌዎችን በአንድነት አቅርቡ፤
ሕፃናትን ሰብስቡ፤
ጡት የሚጠቡትንም አታስቀሩ፤
ሙሽራው እልፍኙን ይተው፣
ሙሽሪትም የጫጕላ ቤቷን ትተው።
17 በእግዚአብሔር ፊት የሚያገለግሉ ካህናት፣
በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አደባባይ መካከል ሆነው ያልቅሱ፤
እንዲህም ይበሉ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አድን፤
ርስትህን በአሕዛብ መካከል መተረቻ፣
መሣቂያና መሣለቂያም አታድርግ፤
ለምንስ በሕዝቦች መካከል፣
‘አምላካቸው ወዴት ነው?’ ይበሉን።”
የእግዚአብሔር መልስ
18እነሆ፤ እግዚአብሔር ስለ ምድሩ ይቀናል#2፥18 ወይም ጌታ ቀንቷል ራርቷል
ስለ ሕዝቡም ይራራል።
19 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል#2፥19 ጌታ መለሰለት
“እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅና ዘይት፣
እስክትጠግቡ ድረስ እሰጣችኋለሁ፤
የሕዝቦች መዘባበቻ አላደርጋችሁም።
20“የሰሜንን ሰራዊት ከእናንተ አርቃለሁ፤
ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር#2፥20 የሙት ባሕር ለማለት ነው።
ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር#2፥20 የሜዲትራንያን ባሕር ለማለት ነው። በማድረግ፣
ወደ ደረቀውና ወደ ባድማው ምድር እገፋዋለሁ፤
ግማቱ ይወጣል፤
ክርፋቱም ይነሣል።”
በርግጥ እርሱ ታላቅ ነገር አድርጓል።
21ምድር ሆይ፤ አትፍሪ፤
ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤
በርግጥ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጓል።
22የዱር እንስሳት ሆይ፤ አትፍሩ፤
መሰማሪያ መስኮቹ ለምልመዋልና፤
ዛፎቹ ፍሬያቸውን አፍርተዋል፤
የበለሱ ዛፍና የወይኑ ተክልም እጅግ አፍርተዋል።
23የጽዮን ሰዎች ሆይ፤ ደስ ይበላችሁ፤
በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ሐሤት አድርጉ፤
የበልግን ዝናብ፣
በጽድቅ ሰጥቷችኋልና#2፥23 ወይም ለጽድቅ መምህር
እንደ ቀድሞውም፣
የበልግንና የጸደይን ዝናብ በብዛት ልኮላችኋል።
24ዐውድማዎቹ በእህል ይሞላሉ፤
መጥመቂያ ጕድጓዶችም በአዲስ የወይን ጠጅና በዘይት ተሞልተው ያፈስሳሉ።
25“በመካከላችሁ የሰደድሁት ታላቁ ሰራዊት፣
ትልልቁ አንበጣና ትንንሹ አንበጣ፣
ሌሎች አንበጦችና የአንበጣው መንጋ#2፥25 በዚህ ክፍል ስለ አንበጦች የሚገልጹት አራት የዕብራይስጥ ቃላት ትክክለኛ ትርጕም አይታወቅም። የበላውን፣
እነዚህ ሁሉ የበሏቸውን ዓመታት ዋጋ እመልስላችኋለሁ።
26እስክትጠግቡ የምትበሉት ብዙ ምግብ ይኖራችኋል፤
ድንቅ ነገሮችን ለእናንተ የሠራውን፣
የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ስም ታመሰግናላችሁ፤
ሕዝቤም ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም።
27ከዚያም እኔ በእስራኤል መካከል እንዳለሁ፣
እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ፣
እንደ እኔም ያለ፣ ሌላ እንደሌለ ታውቃላችሁ፤
ሕዝቤም ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም።
የእግዚአብሔር ቀን
28“ከዚህም በኋላ፣
መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤
ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤
ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፤
ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ።
29በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ እንኳ፣
መንፈሴን አፈስሳለሁ።
30ድንቆችን በሰማያት፣
እንዲሁም በምድር፣
ደምና እሳት፣ የጢስም ዐምድ አሳያለሁ።
31ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣
ፀሓይ ትጨልማለች፤
ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች።
32 የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ፣
እርሱ ይድናል፤
እግዚአብሔርም እንዳለው፣
በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም፣
መድኀኒት ይገኛል፤
ከትሩፋኑም መካከል
እግዚአብሔር የጠራቸው በዚያ ይገኛሉ።”

Currently Selected:

ኢዩኤል 2: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy