YouVersion Logo
Search Icon

ዮሐንስ 10

10
እረኛና መንጋው
1 “እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ጕረኖ በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘልሎ የሚገባ ሌባና ነጣቂ ነው። 2በበሩ የሚገባ ግን እርሱ የበጎቹ እረኛ ነው፤ 3በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። 4የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። 5እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።” 6ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን ምን እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም።
7ስለዚህ ኢየሱስ ዳግም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። 8ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ቀማኞች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም። 9በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል#10፥9 ወይም በደኅና ይጠበቃል፤ ይገባል፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። 10ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።
11 “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ 12ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የእርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሏቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም። 13የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው።
14 “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ 15ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። 16ከዚህ ጕረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። 17መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወድደኛል። 18ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።”
19ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ። 20ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ።
21ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ።
የአይሁድ አለማመን
22በኢየሩሳሌምም የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል#10፥22 ዕብራይስጡ “ኑካ” ይላል። ሆነ፤ ጊዜውም ክረምት ነበረ፤ 23ኢየሱስም በቤተ መቅደስ ግቢ፣ በሰሎሞን መመላለሻ ያልፍ ነበር፤ 24አይሁድም ከብበውት፣ “እስከ መቼ ልባችንን አንጠልጥለህ ታቈየናለህ? አንተ ክርስቶስ#10፥24 ወይም መሲሑ ከሆንህ በግልጽ ንገረን” አሉት።
25ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እኔ ነግሬአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የማደርጋቸው ታምራትም ስለ እኔ ይናገራሉ፤ 26እናንተ ግን በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም፤ 27በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ 28እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም። 29እነርሱን የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል#10፥29 ብዙ የጥንት ቅጆች አባቴ የሰጠኝ ከሁሉ ይበልጣል ይላሉ።፤ ከአባቴም እጅ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም። 30እኔና አብ አንድ ነን።”
31አይሁድ ሊወግሩት እንደ ገና ድንጋይ አነሡ፤ 32ኢየሱስ ግን፣ “ከአብ የሆኑ ብዙ ታላላቅ ታምራትን አሳየኋችሁ፤ ታዲያ ከእነዚህ ስለ የትኛው ትወግሩኛላችሁ?” አላቸው።
33አይሁድም፣ “የምንወግርህ፣ ተራ ሰው ሆነህ ሳለህ፣ ራስህን አምላክ በማድረግ፣ የስድብ ቃል ስለ ተናገርህ ነው እንጂ ከእነዚህ ስለ የትኛውም አይደለም” ብለው መለሱለት።
34ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሕጋችሁ፣ ‘እናንት አማልክት ናችሁ አልሁ’ ተብሎ አልተጻፈምን? 35የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ‘አማልክት’ ካላቸውና መጽሐፍም ሊሻር የማይቻል ከሆነ፣ 36ታዲያ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስላልሁ፣ አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን፣ ተሳድበሃል ብላችሁ ለምን ትወነጅሉኛላችሁ? 37አባቴ የሚያደርገውን ባላደርግ አትመኑኝ፤ 38የማደርገው ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ፣ አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ታምራቱን እመኑ።” 39እንደ ገናም ሊይዙት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አመለጠ።
40ከዚያም ኢየሱስ፣ ቀደም ሲል ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደ ነበረበት፣ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ተመለሰ፤ በዚያም ሰነበተ፤ 41ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “ዮሐንስ አንድም ታምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ነገር ግን ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ። 42በዚያም ስፍራ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ።

Currently Selected:

ዮሐንስ 10: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy