YouVersion Logo
Search Icon

መሳፍንት 2

2
የእግዚአብሔር መልአክ በቦኪም
1 የእግዚአብሔር መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ፤ “ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ ለቀደሙትም አባቶቻችሁ ልሰጣቸው ወደ ማልሁላቸው ምድር አመጣኋችሁ፤ እንዲህም አልሁ፤ ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አላፈርስም፤ 2እናንተም ከዚህች ምድር ነዋሪዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ፤ መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤ እናንተ ግን አልታዘዛችሁኝም፤ ይህን ያደረጋችሁት ለምንድን ነው? 3ስለዚህ አሁንም ከፊታችሁ አሳድጄ እንደማላስወጣቸው እነግራችኋለሁ፤ ነገር ግን እነርሱ የጐን ውጋት፣ አማልክታቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል።”
4 የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤላውያን ሁሉ በተናገረ ጊዜ፣ ሕዝቡ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ 5ያንን ስፍራ ቦኪም#2፥5 ቦኪም ማለት አልቃሽ ማለት ነው። ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ።
ያለ መታዘዝ ውጤት
6ኢያሱ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ምድሪቱን ለመውረስ ወደየርስቱ ሄደ። 7ኢያሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እንዲሁም ከእርሱ በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ያዩ አለቆች በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለከ።
8 የእግዚአብሔር አገልጋይ የነዌ ልጅ ኢያሱ በመቶ ዐሥር ዓመቱ ሞተ። 9እነርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በምትገኘው ከገዓስ ተራራ በስተ ሰሜን ባለችው በራሱ ርስት ላይ በተምናሔሬስ ቀበሩት።
10ያ ሁሉ ትውልድ ወደ አባቶቹ ከተከማቸ በኋላ እግዚአብሔርንም ሆነ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር የማያውቅ ሌላ ትውልድ ተነሣ። 11ከዚያም እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረጉ፤ የበኣል አማልክትንም አመለኩ። 12ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፤ በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን አማልክት ተከተሉ፤ ሰገዱላቸውም። እግዚአብሔርንም አስቈጡት፤ 13እርሱን ትተው በኣልንና አስታሮትን አምልከዋልና 14እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በመቈጣቱ ለሚዘርፏቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸው ላሉ ጠላቶቻቸው ሸጣቸው። 15እስራኤላውያን ለውጊያ በሚወጡበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር አስቀድሞ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረውና እንደ ማለው ይሸነፉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እጅግ ተጨነቁ።
16 እግዚአብሔርም ከእነዚህ ወራሪዎች የሚያድኗቸውን መሳፍንት#2፥16 በዚህም ከ17-19 ባለው ክፍል መሪ ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። አስነሣ፤ 17እስራኤላውያን ግን ሌሎችን አማልክት ተከትለው አመነዘሩ፤ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንታቸውን አልሰሙም። አባቶቻቸው እግዚአብሔርን በመታዘዝ በሄዱበት መንገድ ሳይሆን፣ አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን ሕግ በመከተል ከሄዱበት መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ። 18እግዚአብሔር መሳፍንትን ባሰነሣላቸው ቍጥር ከመስፍኑ ጋር ስለሚሆን፣ እርሱ በሕይወት እስካለ ድረስ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው ያድናቸው ነበር፤ ከጠላቶቻቸው ሥቃይና መከራ ሲደርስባቸው በሚጮኹበት ጊዜ እግዚአብሔር ይራራላቸው ነበር። 19መስፍኑ ከሞተ በኋላ ግን ሕዝቡ ሌሎችን አማልክት በመከተል፣ እነርሱን በማገልገልና በማምለክ ከአባቶቻቸው ይልቅ ወደ ክፉ መንገድ ተመለሱ፤ ክፉ ሥራቸውንና የእልኸኝነት መንገዳቸውንም አይተውም ነበር።
20ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፤ “ይህ ሕዝብ ለቀደሙ አባቶቹ የሰጠሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፈ፣ እኔንም ስላልሰማ፣ 21ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው በምድሪቱ ከነበሩት ሕዝቦች አንዳቸውንም እንኳ በፊታቸው አሳድጄ አላስወጣም። 22ይህን የማደርገውም አባቶቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፣ እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን መንገድ የሚጠብቁ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ እፈትናቸው ዘንድ እነርሱን መሣሪያ ለማድረግ ነው።” 23ስለዚህ እግዚአብሔር እነዚያን ሕዝቦች በዚያው እንዲኖሩ አደረገ፤ በኢያሱ እጅ አሳልፎ በመስጠት ወዲያውኑ አሳድዶ አላስወጣቸውም።

Currently Selected:

መሳፍንት 2: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy