YouVersion Logo
Search Icon

መሳፍንት 14

14
የሳምሶን ጋብቻ
1ሳምሶን ወደ ተምና ወረደ፤ እዚያም አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አየ። 2እንደ ተመለሰም አባቱንና እናቱን፣ “በተምና አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አይቻለሁና አሁኑኑ አጋቡኝ” አላቸው።
3አባቱና እናቱም፣ “ከዘመዶችህ ወይም ከሕዝባችን ሁሉ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት መች ታጣችና ነው ወዳልተገረዙት ፍልስጥኤማውያን ሚስት ፍለጋ የሄድኸው?” አሉት።
ሳምሶንም አባቱን፣ “ልቤን የማረከችው እርሷ ናትና እርሷን አጋባኝ” አለው። 4በዚያን ጊዜ በእስራኤል ላይ ገዦቹ ፍልስጥኤማውያን ስለ ነበሩ፣ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጠብ እንዲፈጠር እግዚአብሔር ሆን ብሎ ያደረገው ነገር መሆኑን አባቱና እናቱ አላወቁም ነበር። 5ከዚያም ሳምሶን ከአባቱና ከእናቱ ጋር ወደ ተምና ወረደ፤ በዚያም ከአንድ የወይን አትክልት ቦታ እንደ ደረሱ፣ ድንገት አንድ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት። 6በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ስለዚህ የፍየል ጠቦት እንደሚገነጣጠል አንበሳውን ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጠለው፤ ያደረገውን ግን ለአባቱም ሆነ ለእናቱ አልነገራቸውም ነበር። 7ወደ ሴቲቱም ወረደ፤ ከእርሷም ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ወደዳት።
8ከጥቂት ቀን በኋላም ሊያገባት ተመለሰ። የአንበሳውንም በድን ለማየት ከመንገድ ዘወር አለ፤ በበድኑም ውስጥ የንብ መንጋ ሰፍሮ ተመለከተ፤ ማርም ነበረበት፤ 9በእጁ ወስዶም መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ከወላጆቹም ጋር እንደ ተገናኘም ከማሩ ሰጣቸው፤ እነርሱም በሉ። ነገር ግን ማሩን የወሰደው ከአንበሳ በድን መሆኑን አልነገራቸውም ነበር።
10የሳምሶን አባት ልጂቱን ሊያይ ወረደ፤ ሳምሶንም በነበረው የሙሽራ ወግ መሠረት በዚያ ግብዣ አደረገ። 11እርሱም ለፍልስጥኤማውያን በታየ ጊዜ፣ ሠላሳ አጃቢዎች ሰጡት።
12ሳምሶን እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ዕንቈቅልሽ እነግራችኋለሁ፤ ታዲያ ፍቺውን በሰርጉ በዓል ሰባት ቀኖች ውስጥ ከሰጣችሁኝ፣ ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳ የክት ልብስ እሰጣችኋለሁ። 13ዕንቈቅልሹን ካልፈታችሁልኝ ግን ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳውን የክት ልብስ እናንተ ትሰጡኛላችሁ።”
እነርሱም፣ “በል ዕንቈቅልሽህን ንገረንና እንስማው” አሉት።
14ሳምሶንም፣
“ከበላተኛው መብል፣
ከብርቱም ጣፋጭ ነገር ወጣ” አላቸው።
እነርሱም እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቈቅልሹን መፍታት አልቻሉም ነበር።
15በአራተኛው#14፥15 አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞችና የሱርስቱ ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን ሰባተኛ ይላል። ቀን የሳምሶንን ሚስት፣ “የዕንቈቅልሹን ፍች እንዲነግረን ባልሽን እስቲ አግባቢልን፤ ያለዚያ አንቺንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ በእሳት እናቃጥላችኋለን፤ ጠርታችሁ የጋበዛችሁን ልትዘርፉን ነው?” አሏት።
16ከዚያ የሳምሶን ሚስት ተንሰቅስቃ እያለቀሰች ከፊቱ በመቅረብ፣ “ለካስ ትጠላኛለህ! በርግጥ አትወደኝም” አለችው።
እርሱም፣ “ይህን ለአባቴም ሆነ ለእናቴ አልነገርኋቸውም፤ ታዲያ ለአንቺ ለምን እነግርሻለሁ?” አላት። 17ሚስቱም በሰርጉ በዓል ሰባት ቀን ሙሉ እያለቀሰች ጨቀጨቀችው፤ አጥብቃ ስለ ነዘነዘችውም በመጨረሻ በሰባተኛው ቀን ነገራት፤ እርሷም በበኩሏ የዕንቈቅልሹን ፍች ለሕዝቧ ነገረች።
18በሰባተኛው ቀን ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት የከተማው ሰዎች፣
“ከማር የጣፈጠ ምን ተገኝቶ?
ከአንበሳስ ወዲያ ብርቱ ከየት መጥቶ!” አሉት።
ሳምሶንም መልሶ፣
“በጊደሬ ባላረሳችሁ፣
እንቈቅልሼንም ባልፈታችሁ” አላቸው።
19ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት፤ ወደ አስቀሎናም ወርዶ ከሰዎቻቸው መካከል ሠላሳውን ገደለ፤ ያላቸውንም ከገፈፈ በኋላ ልብሶቻቸውን አምጥቶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጣቸው። በቍጣ እንደ ነደደም ተነሥቶ ወደ አባቱ ቤት ወጣ። 20የሳምሶንም ሚስት ለሚዜው ተዳረች።

Currently Selected:

መሳፍንት 14: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy