YouVersion Logo
Search Icon

ዘፀአት 24

24
ቃል ኪዳኑ ስለ መጽናቱ
1ከዚያም ሙሴን “አንተና አሮን፣ ናዳብና አብድዩ ከሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ጋር ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ኑ፤ ከሩቅም ስገዱ አለው፤ 2ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሊቀርብ የሚችለው ሙሴ ብቻ ነው። ሌሎቹ መቅረብ የለባቸውም፤ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር መምጣት የለበትም።”
3ሙሴ ወደ ሕዝቡ ሄዶ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃሎችና ሕጎች ሁሉ በነገራቸው ጊዜ በአንድ ድምፅ ሆነው፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” አሉ። 4ከዚያም ሙሴ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ ጻፈ። በማግስቱም ማልዶ ተነሥቶ፣ በተራራው ግርጌ መሠዊያን ሠራ፤ ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤልን ነገዶች የሚወክሉ ዐሥራ ሁለት የድንጋይ ዐምዶችን አቆመ። 5ከዚያም ወጣት ወንድ እስራኤላውያንን ላከ፤ እነርሱም የሚቃጠል መሥዋዕት#24፥5 በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት በመባል ይታወቃል። አቀረቡ፤ ወይፈኖችን የኅብረት መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሠዉ። 6ሙሴ የደሙን እኩሌታ ወስዶ በጐድጓዳ ሳሕኖች አኖረው፤ የቀረውንም እኩሌታ በመሠዊያው ላይ ረጨው። 7ከዚያም የኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ እንታዘዛለን” አሉ።
8ከዚያም ሙሴ ደሙን ወሰደ፤ ሕዝቡም ላይ ረጭቶ፣ “ይህ እነዚህን ቃሎች በሰጠ ጊዜ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባው የቃል ኪዳኑ ደም ነው” አላቸው።
9ሙሴና አሮን፣ ናዳብና አብድዩ እንደዚሁም ሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ወደ ተራራው ወጡ፣ 10የእስራኤልንም አምላክ (ኤሎሂም) አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ብሩህ ሰማይ የጠራ የሰንፔር#24፥10 ወይም፣ ላፒስ ላዘሊ ተብሎ መተርጐም ይችላል። ወለል ነበር። 11ሆኖም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በእስራኤል ሕዝብ አለቆች ላይ እጁን አላነሣባቸውም። እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) አዩ፣ በሉ፤ ጠጡም።
12 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በተራራው ላይ ወደ እኔ ና፤ በዚህም ቈይ፤ እኔም መመሪያ እንዲሆናቸው ሕግና ትእዛዞች የጻፍኩባቸውን የድንጋይ ጽላቶች እሰጥሃለሁ” አለው።
13ከዚያም ሙሴ ከረዳቱ ከኢያሱ ጋር አብሮ ሄደ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ ወጣ። 14እርሱም ሽማግሌዎችን “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቈዩ፤ አሮንና ሖር ከእናንተ ጋር ናቸው፤ ክርክር ያለው ሰው ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ።” አላቸው።
15ሙሴ ወደ ተራራ ሲወጣ ደመናው ተራራውን ሸፈነ፤ 16የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ክብር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፤ ደመናውም ተራራውን እስከ ስድስት ቀን ድረስ ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር (ያህዌ) በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ጠራው። 17ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ክብር በተራራው ጫፍ ላይ እንደሚባላ እሳት ሆኖ ይታይ ነበር። 18ከዚያም ሙሴ ወደ ተራራው ሲወጣ ደመናው ውስጥ ገባ፤ በተራራውም ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ።

Currently Selected:

ዘፀአት 24: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy