YouVersion Logo
Search Icon

አስቴር 1

1
ንግሥት አስጢን ከክብሯ ወረደች
1ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያሉትን አንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች ይገዛ በነበረው በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት እንዲህ ሆነ፤ 2በዚያን ዘመን ንጉሡ ጠረክሲስ የገዛው በሱሳ ግንብ ባለው ንጉሣዊ ዙፋኑ ሆኖ ነበር። 3እርሱም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለመኳንንቱና ለሹማምቱ ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ። በግብዣውም የፋርስና የሜዶን የጦር አዛዦች፣ መሳፍንትና የየአውራጃው መኳንንት ተገኝተው ነበር።
4ለእነርሱም የመንግሥቱን ሰፊ ሀብት፣ የግርማውን ታላቅነትና ክብር አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ሙሉ አሳያቸው። 5እነዚህ ቀናት ካለፉ በኋላ፣ ንጉሡ በሱሳ ግንብ ለነበሩት፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ዙሪያውን በአትክልት በተከበበው አደባባይ ሰባት ቀን የፈጀ ግብዣ አደረገ። 6አደባባዩም ከነጭና ከሰማያዊ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤ እነርሱም የብር ቀለበት በተበጀላቸው፣ ከነጭ በፍታና ከሐምራዊ ቀለም በተሠሩ ገመዶች በዕብነ በረዱ ምሰሶዎች ላይ ተንጠልጥለው ነበር። ነጭና ቀይ ቀለማት ተሰበጣጥረው በተነጠፉበት ወለል ላይ የወርቅና የብር ድንክ ዐልጋዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከዕብነ በረድ፣ ቀስተ ደመና ከሚመስሉ ቀለሞችና ከሌሎች የከበሩ ድንጋዮች የተሠሩ ነበሩ። 7የወይን ጠጁም አንዱ ከሌላው ልዩ በሆነ የወርቅ ዋንጫ ይቀርብ ነበር፤ ከንጉሡም ልግስና የተነሣ የቤተ መንግሥቱ የወይን ጠጅ የተትረፈረፈ ነበር። 8ንጉሡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን ያህል እንዲያቀርቡለት የወይን ጠጅ አሳላፊዎቹን ሁሉ አዝዞ ስለ ነበረ፣ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ ተስተናጋጅ እንዲጠጣ ተፈቅዶለት ነበር።
9ንግሥት አስጢንም በንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት እንደዚሁ ለሴቶች ግብዣ አድርጋ ነበር።
10በሰባተኛው ቀን ንጉሥ ጠረክሲስ ከወይን ጠጁ የተነሣ ደስ ስለ ተሰኘ፣ አገልጋዮቹ የሆኑትን ሰባቱን ጃንደረቦች ምሁማንን፣ ባዛንን፣ ሐርቦናን፣ ገበታን፣ ዘቶልያንን፣ ዜታርንና ከርከስን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ 11ይኸውም ንግሥት አስጢን የደስ ደስ ያላት ነበረችና ውበቷ ለሕዝቡና ለመኳንንቱ እንዲታይ ዘውዷን ጭና ንጉሡ ፊት እንዲያመጧት ነበር። 12አገልጋዮቹ የንጉሡን ትእዛዝ በነገሯት ጊዜ ግን፣ ንግሥት አስጢን መሄድ አልፈለገችም። ከዚያም ንጉሡ በጣም ተቈጣ፤ እጅግም ተናደደ።
13ሕግንና ፍትሕን በተመለከተ የሊቃውንቱን ምክር መጠየቅ በንጉሥ ዘንድ የተለመደ ነበርና፣ ስለ ዘመናት ሁኔታ ዕውቀት ካላቸው ጠቢባን ጋር ተነጋገረበት፤ 14እነዚህ አርቄስዮስ፣ ሼታር፣ አድማታ፣ ተርሺሽ፣ ሜሬስ፣ ማሌሴዓር፣ ምሙካ የተባሉ ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መኳንንት በንጉሡ ዘንድ የተለየ ስፍራና በመንግሥቱም አመራር ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ነበሩ።
15ንጉሡም፣ “በጃንደረቦቹ በኩል የተላከባትን የንጉሥ ጠረክሲስን ትእዛዝ ስላልፈጸመች፣ በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ ምን መደረግ አለበት?” ሲል ጠየቃቸው።
16ከዚያም ምሙካ በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንግሥት አስጢን የበደለችው ንጉሡን ብቻ ሳይሆን፣ መኳንንቱን ሁሉና በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃዎች የሚኖሩትን ሕዝቦች ጭምር ነው። 17ይህ የንግሥቲቱ አድራጎት በሌሎቹ ሁሉ ዘንድ ስለሚሰማ፣ ባሎቻቸውን ይንቃሉ፤ ‘ንጉሥ ጠረክሲስ ንግሥት አስጢን ወደ እርሱ እንድትመጣ ቢያዛትም፣ እርሷ ግን መሄድ አልፈለገችም’ ይላሉ። 18በዚህች በዛሬዪቱም ዕለት የንግሥቲቱን አድራጎት የሰሙ የፋርስና የሜዶን መኳንንት ሚስቶች፣ ለንጉሡ መኳንንት ሁሉ በዚሁ ዐይነት ሊመልሱ ነው፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ማብቂያ የሌለው ንቀትና ጠብ ይፈጠራል።
19“ስለዚህ ነገሩ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፣ አስጢን ወደ ንጉሡ ወደ ጠረክሲስ ዘንድ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ እንዳትገባ ንጉሣዊ ዐዋጅ ይውጣ፤ ይህም የማይሻር ሆኖ በፋርስና በሜዶን ሕጎች ይጻፍ፤ እንዲሁም ንጉሡ የእቴጌነቷን ክብር ከእርሷ ለምትሻል ለሌላዪቱ ይስጥ። 20ከዚያም የንጉሡ ዐዋጅ በሰፊው ግዛቱ ሁሉ ሲነገር፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉት ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ያከብራሉ።”
21ንጉሡና መኳንንቱ ሁሉ በዚህ ምክር ተደሰቱ፤ ንጉሡም ምሙካ ያቀረበውን ሐሳብ በሥራ ላይ አዋለው። 22እያንዳንዱ ሰው በራሱ ቤተ ሰብ ላይ ገዥ እንዲሆን መልእክት አስተላለፈ፤ መልእክቱም ለየአውራጃዎቹ በየራሳቸው ጽሑፍና ለእያንዳንዱ ሕዝብ በየራሱ ቋንቋ ተጽፎ በግዛቱ ሁሉ ተበተነ።

Currently Selected:

አስቴር 1: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy