YouVersion Logo
Search Icon

ዘዳግም 7

7
አሕዛብን ማስወጣት
1አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህና ብዙዎችን ከአንተ የሚበልጡ ታላላቆችና ብርቱዎች የሆኑትን ሰባቱን አሕዛብ፦ ኬጢያውያንን፤ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ በሚያስወጣቸው ጊዜ፣ 2አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጠህና አንተም ድል ባደረግሃቸው ጊዜ፣ ሁሉንም ፈጽመህ ደምስሳቸው#7፥2 በዚህና በቍጥር 26 ላይ የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።፤ ከእነርሱ ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፤ አትራራላቸውም። 3ከእነርሱ ጋራ ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ፤ 4ምክንያቱም እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉና ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላይህ ነድዶ፣ ፈጥኖ ስለሚያጠፋህ ነው። 5እንግዲህ በእነርሱ ላይ የምታደርጉት ይህ ነው፤ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን#7፥5 እዚህ ላይና በዚሁ መጽሐፍ በሌላ ስፍራ አሼራ የምትባለውን ጣዖት ምስል የሚያመለክት ነው። ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን ቍረጡ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ። 6አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ።
7 እግዚአብሔር እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ ቍጥራችሁማ ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ አነስተኛ ነበር። 8ነገር ግን እናንተን በብርቱ እጅ ያወጣችሁ፣ ከባርነት ምድርና ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን መዳፍ የተቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር እናንተን ስለ ወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ ነው። 9ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወድዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ ነው። 10ነገር ግን፣
የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ይበቀላቸዋል፤
የሚጠሉትን ዐይናቸው እያየ ለመበቀል አይዘገይም።
11ስለዚህ በዛሬው ቀን የምሰጥህን ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕግጋቱን ለመከተል ጥንቃቄ አድርግ።
12እነዚህን ሕግጋት ብታዳምጥና በጥንቃቄ ብትጠብቃቸው፣ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ እንደ ማለላቸው ከአንተ ጋራ የገባውን የፍቅር ኪዳኑን ይጠብቃል። 13ይወድድሃል፤ ይባርክሃል፤ ያበዛሃልም። ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የማሕፀንህን ፍሬ፣ የምድርህን ሰብል፣ እህልህን፣ አዲሱን ወይንና ዘይት፤ የከብት መንጋህን ጥጆች፣ የበግና የፍየል መንጋህን ግልገሎች ይባርካል። 14ከሕዝቦች ሁሉ የበለጠ አንተ ትባረካለህ፤ ከአንተ ወይም ከከብቶችህ መካከል የማይወልድ ወንድ ወይም ሴት አይኖርም። 15እግዚአብሔር ከማናቸውም በሽታ ነጻ ያደርግሃል፤ በግብጽ የምታውቃቸውን እነዚያን አሠቃቂ በሽታዎች በሚጠሉህ ሁሉ ላይ እንጂ በአንተ ላይ አያመጣብህም። 16አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ማጥፋት አለብህ፤ አትዘንላቸው፤ ወጥመድ ስለሚሆኑብህም አማልክታቸውን አታምልክ።
17“እነዚህ አሕዛብ ከእኛ ይልቅ ጠንካሮች ስለ ሆኑ፣ እንዴት አድርገን እናስወጣቸዋለን?” ብለህ በልብህ ታስብ ይሆናል። 18ነገር ግን አትፍራቸው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብጽ ሁሉ ላይ ያደረገውን በሚገባ አስታውስ። 19ታላላቅ ፈተናዎችን፣ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን አምላክህ እግዚአብሔር አንተን ያወጣበትን ብርቱ እጅና የተዘረጋች ክንድ በገዛ ዐይንህ አይተሃል። አምላክህ እግዚአብሔር አሁን በምትፈራቸው ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያንኑ ያደርጋል። 20ይልቁንም አምላክህ እግዚአብሔር በሕይወት ተርፈው፣ ከአንተ የተደበቁት እንኳ እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ተርብ ይሰድድባቸዋል። 21በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ ስለ ሆነ አያስደንግጡህ። 22አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ጥቂት በጥቂት ከፊትህ ያስወጣቸዋል፤ የዱር አራዊቱ ቍጥር በአካባቢህ እንዳይበራከት ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማጥፋት አይፈቀድልህም፤ 23አምላክህ እግዚአብሔር ግን እስኪጠፉ ድረስ ከባድ ትርምስ ፈጥሮባቸው በእጅህ አሳልፎ ይሰጥሃል። 24ነገሥታታቸውን በእጅህ ይጥላቸዋል፤ ስማቸውንም ከሰማይ በታች ታጠፋለህ። እስክትደመስሳቸው ድረስ አንተን መቋቋም የሚችል አንድም ሰው የለም። 25የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ ያሰናክልሃል። 26አስጸያፊ ነገርን ወደ ቤትህ ወይም ወደ ራስህ አታምጣ፤ አለዚያ አንተም እንደ እርሱ ለጥፋት ትዳረጋለህ፤ ፈጽመህ ጥላው፤ ተጸየፈውም፤ ለጥፋት የተለየ ነውና።

Currently Selected:

ዘዳግም 7: NASV

Highlight

Copy

Compare

Share

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in