YouVersion Logo
Search Icon

ዘዳግም 30

30
ወደ እግዚአብሔር በመመለስ የሚገኝ በረከት
1በፊትህ ያስቀመጥሁት ይህ በረከትና መርገም ሁሉ በአንተ ላይ ሲመጣና አምላክህ እግዚአብሔር በትኖህ በምትኖርበት አሕዛብ መካከል ሆነህ ወደ ልብህ ተመልሰህ ነገሮቹን በምታስተውልበት ጊዜ፣ 2እንዲሁም ዛሬ እኔ በማዝዝህ ሁሉ መሠረት አንተና ልጆችህ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመልሳችሁ በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ እርሱን ስትታዘዙ፣ 3አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልስልሃል#30፥3 ወይም፣ ከግዞት ይመልስሃል።፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከልም እንደ ገና ይሰበስብሃል። 4ከሰማይ በታች እጅግ ሩቅ ወደ ሆነ ምድር ብትጋዝ እንኳ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፤ መልሶም ያመጣሃል። 5አምላክህን እግዚአብሔር የአባቶችህ ወደሆነችው ምድር ያመጣሃል፤ አንተም ትወርሳታለህ። ከአባቶችህ ይበልጥ ያበለጽግሃል፤ ያበዛሃልም። 6አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንድትወድደው፣ በሕይወትም እንድትኖር፣ አምላክህ እግዚአብሔር የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል። 7አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ርግማን ሁሉ በሚጠሉህና በሚያሳድዱህ ጠላቶችህ ላይ ያደርገዋል። 8አንተም ተመልሰህ ለእግዚአብሔር ትታዘዛለህ፤ ዛሬ እኔ የማዝዝህን ትእዛዝ ሁሉ ትጠብቃለህ። 9ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉና በወገብህ ፍሬ፣ በእንስሳትህ ግልገሎችና በምድርህ ሰብል እጅግ ያበለጽግሃል። በአባቶችህ ደስ እንደ ተሠኘ ሁሉ፣ እግዚአብሔር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋልና። 10ይህም የሚሆነው፣ አምላክህን እግዚአብሔርን ከታዘዝህና በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዐቱን በመጠበቅ፣ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ስትመለስ ነው።
ሕይወትን ወይም ሞትን ስለ መምረጥ
11በዛሬው ዕለት የምሰጥህ ትእዛዝ ይህን ያህል አስቸጋሪ ወይም ከአንተ የራቀች አይደለችም። 12“እንድንፈጽማት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ፣ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?” እንዳትል፣ በላይ በሰማይ አይደለችም። 13ደግሞም፣ “እንድናደርጋት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ፣ ማን ባሕሩን ይሻገራል?” እንዳትልም፣ ከባሕር ማዶ አይደለችም። 14ነገር ግን ቃሉ ለአንተ በጣም ቅርብ ነው፤ ታደርገውም ዘንድ በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው።
15እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትንና በረከትን፣ ሞትንና ጥፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ። 16አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድድ፣ በመንገዱም እንድትሄድና ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን እንድትጠብቅ አዝዝሃለሁ፤ ከዚያም በሕይወት ትኖራለህ፤ ትበዛለህም፤ አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በምትገባበት ምድር ይባርክሃል።
17ዳሩ ግን ልብህ ወደ ኋላ ቢመለስና ባትታዘዝ፣ ለሌሎች አማልክት ለመስገድ ብትታለልና ብታመልካቸው፣ 18በርግጥ እንደምትጠፉ እኔ በዛሬው ዕለት እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ብዙ አትኖሩባትም።
19ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ 20ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትወድድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከርሱ ጋራ እንድትጣበቅ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወትህ ነው፤ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ ሊሰጣቸው በማለላቸው ምድር ረዥም ዕድሜ ይሰጥሃል።

Currently Selected:

ዘዳግም 30: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in