YouVersion Logo
Search Icon

ዘዳግም 26

26
ዐሥራትና በኵራት
1አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር ስትገባ፣ ስትወርሳትና ስትኖርባት፣ 2አምላክህ እግዚአብሔር ከሚሰጥህ ምድር ከምትሰበስበው ሰብል ሁሉ፣ በኵራት ወስደህ በቅርጫት ውስጥ አድርገው፤ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ፤ 3በዚያም ወቅት ለሚያገለግለው ካህን፣ “እግዚአብሔር ለእኛ ሊሰጠን ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር እንደ ገባሁ ዛሬ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እናገራለሁ” በለው። 4ካህኑም ቅርጫቱን ከእጅህ ተቀብሎ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ለፊት ያስቀምጠዋል። 5አንተም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብለህ ትናገራለህ፤ “አባቴ ዘላን ሶርያዊ ነበር፤ ከጥቂት ሰዎችም ጋራ ወደ ግብጽ ወረደ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ ታላቅ፣ ኀያልና ቍጥሩ የበዛ ሕዝብ ሆነ። 6ግብጻውያን ግን ከባድ ሥራ በማሠራት አንገላቱን፤ አሠቃዩንም። 7ከዚያ በኋላ የአባቶቻችን አምላክ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ጩኸታችንን ሰማ፤ ጕስቍልናችንን፣ ድካማችንንና የተፈጸመብንን ግፍ ተመለከተ። 8ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ፣ በታላቅ ድንጋጤ፣ በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ከግብጽ አወጣን። 9ወደዚህ ስፍራ አመጣን፤ ማርና ወተት የምታፈስሰውን ይህችን ምድር ሰጠን፤ 10አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ እነሆ፤ አንተ የሰጠኸኝን የምድሪቱን በኵራት አምጥቻለሁ።” ቅርጫቱንም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት አስቀምጠው፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ስገድ። 11ከዚያም አንተ፣ ሌዋዊውና በመካከልህ የሚኖረው መጻተኛ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ይበላችሁ።
12የዐሥራት ዓመት የሆነውን የሦስተኛውን ዓመት ምርት አንድ ዐሥረኛ ለይተህ ካወጣህ በኋላ በየከተሞችህ ውስጥ በልተው እንዲጠግቡ፣ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ስጣቸው፤ 13ከዚያ በኋላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲህ በል፤ “በሰጠኸኝ ትእዛዝ መሠረት የተቀደሰውን ክፍል ከቤቴ አውጥቼ ለሌዋዊው፣ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ሰጥቻለሁ። ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ አንዱንም አልረሳሁም። 14በሐዘን ላይ ሳለሁ፣ ከተቀደሰው ክፍል ላይ ምንም አልበላሁም፤ ባልነጻሁበትም ጊዜ ከዚሁ ላይ ያነሣሁትም ሆነ ለሙታን ያቀረብሁት ምንም ነገር የለም፤ አምላኬን እግዚአብሔርን ታዝዣለሁ፤ ያዘዝኸኝንም ሁሉ ፈጽሜአለሁ። 15ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንና ለአባቶቻችን በመሐላ ቃል በገባኸው መሠረት፣ ለእኛ የሰጠኸንን ይህችን ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር ባርክ።”
የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ስለ መጠበቅ
16አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዐትና ሕግ ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ ያዝዝሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህ፣ በፍጹምም ነፍስህ ትፈጽመው ዘንድ ተጠንቀቅ። 17እግዚአብሔር አምላክህ እንደ ሆነ በመንገዱም እንደምትሄድ፣ ሥርዐቱን፣ ትእዛዙንና ሕጉን እንደምትጠብቅና እንደምትታዘዝለት በዛሬዪቱ ዕለት ተናግረሃል። 18እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት አንተ፣ ሕዝቡና ርስቱ መሆንህን፣ ትእዛዙንም ሁሉ እንደምትጠብቅ በዛሬው ዕለት ተናግሯል። 19ከፈጠራቸው ሕዝቦች ሁሉ በላይ በምስጋና፣ በስም፣ በክብርም ከፍ እንደሚያደርግህና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ እንደምትሆን ተናግሯል።

Currently Selected:

ዘዳግም 26: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in