YouVersion Logo
Search Icon

2 ነገሥት 23

23
ኢዮስያስ ኪዳኑን ዐደሰ
23፥1-3 ተጓ ምብ – 2ዜና 34፥29-32
23፥4-20 ተጓ ምብ – 2ዜና 34፥3-733
23፥21-23 ተጓ ምብ – 2ዜና 35፥135፥18-19
23፥28-30 ተጓ ምብ – 2ዜና 35፥20–36፥1
1ከዚያም ንጉሡ ልኮ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች በአንድ ላይ ሰበሰበ። 2ንጉሡም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ፣ የኢየሩሳሌምን ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ፣ ካህናቱንና ነቢያቱን ሁሉ ከልጅ እስከ ዐዋቂ አንድም ሰው ሳይቀር ይዞ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል በሙሉ በጆሯቸው እንዲሰሙት አነበበላቸው። 3ንጉሡም በዐምዱ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እግዚአብሔርን እንደሚከተል ትእዛዞቹን፣ ደንቦቹን፣ ሥርዐቶቹን በፍጹም ልቡና በፍጹምም ነፍሱ እንደሚጠብቅ፣ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን ኪዳን እንደሚያጸና በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን አደሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ ቃል ኪዳን ገቡ።
4ንጉሡም ለበኣል፣ ለአሼራና ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ የተሠሩትን የመገልገያ ዕቃዎች በሙሉ፣ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲያወጡ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን በሁለተኛ ማዕርግ ያሉትን ካህናትና የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች አዘዘ። ዕቃዎቹንም ከኢየሩሳሌም ውጭ በቄድሮን ሸለቆ ሜዳ ላይ አቃጠላቸው፤ ዐመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው። 5በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሚገኙ ኰረብቶች ላይ ዕጣን እንዲያጥኑ የይሁዳ ነገሥታት የሾሟቸውን የጣዖት ካህናት አባረረ እንዲሁም ለበኣል፣ ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት የሚያጥኑትን አስወገደ። 6የአሼራንም ምስል ዐምድ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አውጥቶ ከኢየሩሳሌም ውጭ ወዳለው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ አቃጠለው፤ አድቅቆ ፈጭቶም በሕዝቡ መቃብር ላይ በተነው። 7እንዲሁም ስለ አምልኮ ባዕድ ሥርዐት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ክፍሎችና ሴቶች ለአሼራ መጋረጃ የሚፈትሉባቸውን ክፍሎች አፈረሰ።
8ኢዮስያስ የቤተ ጣዖት ካህናትን ሁሉ ከይሁዳ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም አወጣቸው፤ ከጌባዕ ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፣ ካህናቱ ዕጣን ያጥኑባቸው የነበሩትን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራዎችን አረከሰ። ከከተማዪቱ በር በስተግራ በኩል፣ በከተማዪቱ ገዥ በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን ማምለኪያ ስፍራዎች#23፥8 ወይም፣ ከፍተኛ ቦታዎች አፈረሰ። 9የየኰረብታው ማምለኪያ ካህናት ኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ባያገለግሉም እንኳ ከካህናት ወንድሞቻቸው ጋራ ቂጣ ይበሉ ነበር።
10በሄኖም ሸለቆ የነበረውን ቶፌት የተባለውን ማምለኪያ አረከሰ፤ ይኸውም ማንም ሰው ወንድ ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዳያቀርብበት#23፥10 ወይም ወንድ ወይም ሴት ልጁን የገደለ ነው። 11የይሁዳ ነገሥታት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ ላይ ለፀሓይ አምልኮ የሰጧቸውን ፈረሶች ከዚያ አስወገደ። እነዚህም ናታን ሜሌክ በተባለ በአንድ ሹም ቤት አጠገብ በአደባባዩ ላይ ነበሩ። ኢዮስያስም ለፀሓይ አምልኮ የተሰጡትን ሠረገሎች አቃጠለ።
12የይሁዳ ነገሥታት በላይኛው የአካዝ እልፍኝ አጠገብ በሰገነቱ ላይ ያቆሟቸውን መሠዊያዎች፣ ምናሴም በሁለቱ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ ያሠራቸውን መሠዊያዎች አስወገደ፤ ስብርብራቸውን አወጣ፤ ድቃቂውንም አንሥቶ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣለው። 13እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ከርኩሰት ኰረብታ በስተ ደቡብ የነበሩትን የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን የርኩሰት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓብ ሕዝቦች የርኩሰት አምላክ ለካሞሽ፣ ለአሞን ሕዝቦች የርኩሰት አምላክ ለሚልኮም ያሠራቸውን የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎች ንጉሡ አረከሰ። 14አሁንም ኢዮስያስ ማምለኪያ የድንጋይ ሐውልቶችን ሰባበረ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈራረጠ፤ ስፍራውንም በሞቱ ሰዎች ዐጥንት ሞላው።
15እስራኤልን ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም የተሠራውን መሠዊያ፣ በቤቴል የነበረውን ያን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራ፣ መሠዊያው ያለበትን ያን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራ እንኳ እንደዚሁ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹን ሰባበረ፤ እንደ ዱቄትም አደቀቃቸው፤ የአሼራንም ምስል ዐምድ አቃጠለ። 16ኢዮስያስ ዘወር ሲል በኰረብታው ላይ የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ዐፅሞቹንም ከየመቃብሩ አስወጣ፤ ያ የእግዚአብሔር ሰው አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ መሠዊያውን ለማርከስ ሲል ዐፅሞቹን በላዩ ላይ አቃጠለበት።
17ንጉሡም፣ “ያ የማየው የመቃብር ሐውልት የማን ነው?” ሲል ጠየቀ።
የከተማዪቱም ሰዎች፣ “ከይሁዳ መጥቶ አሁን አንተ ያደረግኸውን ነገር ሁሉ በቤቴል መሠዊያ ላይ እንደሚደርስ የተናገረ የዚያ የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው” አሉት።
18ኢዮስያስም፣ “በሉ እንዳለ ተዉት፤ ዐፅሙን ማንም ሰው ከቦታው እንዳያንቀሳቅሰው” አለ፤ ስለዚህ የእርሱንና ከሰማርያ የመጣውን ነቢይ ዐፅም ሳይነኩ እንዳለ ተውት።
19ኢዮስያስም በቤቴል እንዳደረገው ሁሉ በሰማርያም ከተሞች ኰረብቶች ላይ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትንና እግዚአብሔርን ያስቈጡበትን ቤተ ጣዖቶች ሁሉ አስወገደ፤ አረከሳቸውም። 20ኢዮስያስ እነዚያን የየኰረብታውን ማምለኪያ ቦታ ካህናትን ሁሉ፣ በየመሠዊያው ላይ ዐረዳቸው፤ በመሠዊያዎቹ ላይ የሰው ዐፅም አቃጠለ፣ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
21ንጉሡም መላውን ሕዝብ፣ “በዚህ በኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብሩ” ብሎ አዘዘ። 22እስራኤልን ከመሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ፣ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ፣ እንደዚህ ያለ ፋሲካ መቼም ተከብሮ አያውቅም። 23በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ግን ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተከበረ።
24ከዚህም በቀር ኢዮስያስ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን፣ የየቤተ ሰቡ ሰውን አማልክት፣ ጣዖታትን እንዲሁም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የተገኙትን ሌሎች አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ አስወገደ፤ ይህን ያደረገውም ካህኑ ኬልቅያስ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈው የሕጉ ቃል ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው። 25በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱ፣ በፍጹም ኀይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ፣ እንደ ኢዮስያስ ያለ ንጉሥ፣ ከርሱ በፊትም ሆነ ከርሱ በኋላ ፈጽሞ አልተነሣም።
26ይህም ሆኖ እንኳ ለቍጣ እንዲነሣሣ ምናሴ ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የተነሣ፣ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከአስፈሪው ቍጣው ገና አልበረደም ነበር። 27ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “እስራኤልን እንዳስወገድሁ ሁሉ ይሁዳንም ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’#23፥27 1ነገ 8፥29 ይመ። ብዬ የተናገርሁለትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ” አለ።
28በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
29ኢዮስያስ ንጉሥ በነበረበት ዘመን የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ የአሦርን ንጉሥ ለመርዳት ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጥቶ ነበር፤ ንጉሥ ኢዮስያስም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ፤ ሆኖም ፈርዖን ኒካዑ ፊት ለፊት ገጥሞት መጊዶ ላይ ገደለው። 30የኢዮስያስም አገልጋዮች ከመጊዶ ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው በገዛ መቃብሩ ቀበሩት። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአካዝን ወስደው ቀቡት፤ በአባቱም ምትክ አነገሡት።
የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአካዝ
23፥31-34 ተጓ ምብ – 2ዜና 36፥2-4
31ኢዮአካዝ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ገዛ። እናቱ አሚጣል ትባላለች፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 32አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 33በኢየሩሳሌም ተቀምጦ እንዳይገዛም ፈርዖን ኒካዑ በሐማት ምድር ሪብላ በምትባል ቦታ አሰረው#23፥33 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን (2ዜና 36፥3 ይመ)፣ ኒካዑ በሐማት ምድር ሪብላ በምትባል ላይ አስወገደው።፤ በአገሩም ላይ አንድ መቶ መክሊት#23፥33 3.4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ብርና አንድ መክሊት#23፥33 34 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ወርቅ ግብር ጣለበት። 34ፈርዖን ኒካዑ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ እግር አነገሠው፤ ኤልያቄም የተባለ ስሙንም ለውጦ ኢዮአቄም አለው። ነገር ግን ኢዮአካዝን በምርኮ ወደ ግብጽ ወሰደው፤ እርሱም በዚያ ሞተ። 35ኢዮአቄምም ፈርዖን ኒካዑ የጠየቀውን ብርና ወርቅ ከፈለ፤ ይህን ለማድረግም የመሬት ግብር ጣለ፤ የአገሩም ሰዎች እንደ ገቢው መጠን ብሩንና ወርቁን እንዲከፍሉ አደረገ።
ኢዮአቄም የይሁዳ ንጉሥ
23፥36–24፥124፥5-6 ተጓ ምብ – 2ዜና 36፥5-8
36ኢዮአቄም በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ ዘቢዳ ትባላለች፤ እርሷም የሩማ ተወላጅ የፈዳያ ልጅ ነበረች። 37አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።

Currently Selected:

2 ነገሥት 23: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in