YouVersion Logo
Search Icon

1 ሳሙኤል 1

1
የሳሙኤል መወለድ
1በተራራማው በኤፍሬም አገር በአርማቴም መሴፋ የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ የኤያሬምኤል ልጅ፣ የኢሊዩ ልጅ፣ የቶሑ ልጅ፣ የናሲብ ልጅ፣ ነበረ። 2እርሱም አንዲቱ ሐና፣ ሌላዪቱ ፍናና የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ፍናና ልጆች ሲኖሯት፣ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም።
3ያም ሰው ሁሉን ቻይ ለሆነው ለእግዚአብሔር ለመስገድና መሥዋዕት ለመሠዋት በየዓመቱ ከሚኖርበት ከተማ ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር። በዚያም ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ የእግዚአብሔር ካህናት ነበሩ። 4ሕልቃና ወደ ሴሎ ሄዶ መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቿ ሁሉ ከሥጋው ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር። 5ሐናን ግን ይወድዳት ስለ ነበር፣ ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ማሕፀኗን ዘግቶት ነበር። 6እግዚአብሔር ማሕፀኗን ስለ ዘጋም ጣውንቷ ታስቈጣት፣ ታበሳጫትም ነበር። 7ይህም በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ ሐና ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ታበሳጫት ነበር። 8ባሏ ሕልቃናም እርሷን፣ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር።
9አንድ ጊዜ በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ#1፥9 የማደሪያ ድንኳን ማለት ነው። መቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። 10ሐናም በነፍሷ ተመርራ አብዝታ በማልቀስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። 11እንዲህም ብላ ስእለት ተሳለች፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም።”
12ሐና ባለማቋረጥ ወደ እግዚአብሔር በጸለየች ጊዜ፣ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር። 13እርሷም በልቧ ትጸልይ ስለ ነበር፤ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ ድምፅዋ አይሰማም ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች አድርጎ ቈጠራት። 14እርሱም “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” አላት።
15ሐናም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ሰክሬ አይደለም፤ እኔ ልቧ ክፉኛ የታወከባት ሴት ነኝ፤ ልቤን በእግዚአብሔር ፊት አፈሰስሁ እንጂ፣ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም። 16ይህን ያህል ጊዜ የጸለይሁት ከባድ ከሆነው ጭንቀቴና ሐዘኔ የተነሣ ስለሆነ፣ አገልጋይህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ።”
17ዔሊም፣ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ይስጥሽ” ሲል መለሰላት።
18እርሷም፣ “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለች፤ ከዚያም መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።
19በማግስቱም ጧት ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋር ተኛ፤ እግዚአብሔርም ዐሰባት፤ 20ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም፤ “ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ” ስትል ሳሙኤል#1፥20 በዕብራይስጡ ሳሙኤል የሚለው ቃል ድምፅ እግዚአብሔር ሰማ ከሚለው ሐረግ ጋር ይመሳሰላል። አለችው።
ሐና ሳሙኤልን ለእግዚአብሔር ሰጠች
21ሰውየውም ሕልቃና ለእግዚአብሔር ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋት ስእለቱን ለማድረስ ቤተ ሰቡን ሁሉ ይዞ ወደ ሴሎ ወጣ። 22ሐና ግን አልሄደችም፤ እርሷም ባሏን፣ “ሕፃኑ ጡት ከተወ በኋላ፣ ወስጄ በእግዚአብሔር ፊት አቀርበዋለሁ፤ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜም በዚያ ይኖራል” አለችው።
23ባሏ ሕልቃናም፣ “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ፤ ጡት እስክታስጥዪው ድረስ እዚሁ ቈዪ፤ ብቻ እግዚአብሔር ቃሉን#1፥23 የሙት ባሕር ጥቅልል፣ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርስቱ ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን ቃልሽን ይላል። ያጽናልሽ” አላት። ስለዚህ ሐና ሕፃኑን ጡት እስክታስጥለው ድረስ እያጠባችው በቤቷ ተቀመጠች።
24ልጁ ጡት በተወ ጊዜ ከእርሱ ጋር አንድ የሦስት ዓመት ወይፈን#1፥24 የሙት ባሕር ጥቅልል፤ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርቱ ትርጕም ከዚህ፤ ጋር ይስማማል የማስሬቱ ቅጅ ግን ሦስት ወይፈን ይላል።፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያ#1፥24 22 ሊትር ያህል ነው። ዱቄትና አንድ አቍማዳ የወይን ጠጅ ወስዳ፣ በሴሎ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጣችው፣ ልጁም ገና ሕፃን ነበረ። 25ወይፈኑን ካረዱ በኋላም ልጁን ወደ ዔሊ አቀረቡት። 26ሐናም ዔሊን እንዲህ አለችው፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በነፍስህ እምላለሁ፤ እዚህ ቦታ ላይ በአጠገብህ ቆማ ወደ እግዚአብሔር ስትጸልይ የነበረች ያች ሴት እኔ ነኝ። 27ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸለይሁ፤ እግዚአብሔርም የለመንሁትን ሰጠኝ። 28ስለዚህ እኔም ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ይሆናል።” እርሱም በዚያ ለእግዚአብሔር ሰገደ።

Currently Selected:

1 ሳሙኤል 1: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy