1 ነገሥት 4
4
የሰሎሞን ሹማምት
1ንጉሥ ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ።
2ዋና ዋናዎቹ ሹማምቱም እነዚህ ነበሩ፤
የሳዶቅ ልጅ ዓዛርያስ፣ ካህን፤
3የሺሻ ልጆች ኤሊሖሬፍና አኪያ፣ ጸሓፊዎች፤
የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ፣ ታሪክ ጸሓፊ፤
4የዮዳሄ ልጅ በናያስ፣ የሰራዊቱ ዋና አዛዥ፤
ሳዶቅና አብያታር፣ ካህናት፤
5የናታን ልጅ ዓዛርያስ፣ የአውራጃ ገዦች የበላይ ኀላፊ፤
የናታን ልጅ ዛቡድ፣ ካህንና የንጉሡ የቅርብ አማካሪ፤
6አሒሳር፣ የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፤
የዓብዳ ልጅ አዶኒራም የግዳጅ ሥራ ተቈጣጣሪ።
7እንዲሁም ሰሎሞን ለንጉሡና ለንጉሡ ቤት የሚሆነውን ቀለብ ከመላው እስራኤል የሚሰበስቡ ዐሥራ ሁለት የአውራጃ ገዦች ነበሩት፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው በዓመት ውስጥ የወር ቀለብ የሚያቀርቡ ነበሩ።
8ስማቸውም እንደሚከተለው ነው፤
ቤንሑር፣ በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር፤
9ቤንጼቄር፣ በማቃጽ፣ በሻዓልቢም፣ በቤትሳሚስ፣ በኤሎንቤትሐናን፤
10ቤንሔሴድ፣ በአሩቦት ውስጥ የሚገኙት ሦኮንና የኦፌር አገር በሙሉ የርሱ ነበር፤
11ቤን አሚናዳብ፤ በናፎት ዶር፣ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ጣፈትን አግብቶ የነበረ ነው፤#4፥11 ወይም በናፎት ቁመት ተብሎ ሊተረጐም ይችላል።
12የአሒሉድ ልጅ በዓና፣ በታዕናክና በመጊዶ እንዲሁም ከጻርታን ቀጥሎ ቍልቍል እስከ ኢይዝራኤል ባለው በቤትሳን ሁሉ፣ ከዚያም ዮቅምዓምን ተሻግሮ እስከ አቤልምሖላና ድረስ፣
13ቤንጌበር፣ በገለዓድ ራሞት ከተማ እዚያው ገለዓድ ውስጥ የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች፣ በባሳንም የአርጎብ አውራጃ እንዲሁም በሮቻቸው የናስ መወርወሪያ በሆኑ ስድሳ ባለ ቅጥር ታላላቅ ከተሞች፤
14የዒዶ ልጅ አሒናዳብ፤ በመሃናይም፣
15አኪማአስ በንፍታሌም፣ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባስማትን አግብቶ የነበረ ነው፤
16የኩሲ ልጅ በዓና፤ በአሴርና በበዓሎት፣
17የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሳኮር፣
18የኤላ ልጅ ሳሚ በብንያም፣
19የኡሪ ልጅ ጌበር፣ በገለዓድ፤ በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፣ በባሳን ንጉሥ በዐግ አገር፣ እርሱም የአውራጃው ብቸኛ ገዥ ነበር።
ለሰሎሞን በየቀኑ የሚገባለት ቀለብ
20የይሁዳና የእስራኤል ሕዝቦች ብዛታቸው እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ሆነ፤ ይበሉ፣ ይጠጡና ይደሰቱም ነበር። 21ሰሎሞንም ከወንዙ#4፥21 በዚህና በ24 ላይ የተጠቀሰው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው። አንሥቶ እስከ ፍልስጥኤማውያን ምድር፣ ከዚያም እስከ ግብጽ ዳርቻ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ ገዛ፤ እነዚህም አገሮች ግብር አመጡለት፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ተገዙለት።
22ለሰሎሞን በየቀኑ የሚገባለትም ቀለብ ይህ ነበር፤ ሠላሳ ኮር#4፥22 5500 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ማለፊያ ዱቄት፣ ስድሳ ኮር#4፥22 11000 ኪሎ ግራም ያህል ነው። መናኛ ዱቄት፣ 23ዐሥር ቅልብ ሰንጋዎች፣ ሃያ ግጦሽ መሬት ላይ የሚውሉ በሬዎች፣ መቶ በግና ፍየል እንዲሁም ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ የበረሓ ፍየልና ምርጥ አዕዋፍ። 24ከወንዙ በስተ ምዕራብ፣ ከቲፍሳ እስከ ጋዛ ያሉትን መንግሥታት ስለ ገዛ፣ በሁሉም አቅጣጫ ሰላም ሆኖለት ነበር። 25በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር ያለ ሥጋት ለመኖር በቃ።
26ሰሎሞን ሠረገላ የሚጐትቱ ፈረሶች የሚያድሩበት አራት ሺሕ ጋጣና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች#4፥26 ዕብራይስጡና አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች አርባ (በተጨማሪም 2ዜና 9፥25 ይመ) ይላሉ። ነበሩት#4፥26 ወይም ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይችላል።።
27የየአውራጃው ሹማምትም በየወር ተራቸው ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ማእድ የሚቀርቡትን ሁሉ ምንም ሳያጓድሉ ይቀልቡ ነበር፤ 28እንዲሁም ለሠረገላ ፈረሶችና ለፈጣን ፈረሶች የተመደበውን ገብስና ጭድ ከተፈለገው ቦታ ድረስ ያመጡ ነበር።
የሰሎሞን ጥበብ
29አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን እንዲሁም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው። 30የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብጽም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር፤ 31እርሱም ከማንም ሰው ይልቅ ጥበበኛ ነበር፣ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታን፣ ከማሖል ልጆች ከሄማንና ከከልቀድ ደግሞም ከደራል ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት አሕዛብ ሁሉ ተሰማ። 32እርሱም ሦስት ሺሕ ምሳሌዎችን ተናገረ፤ የመሓልዩም ቍጥር ሺሕ ዐምስት ነበር። 33ከሊባኖስ ዝግባ አንሥቶ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ ስለ ዕፀዋት ተናግሯል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣ ስለ ወፎች፣ በምድር ላይ ስለሚሳቡ ፍጥረታትና ስለ ዓሦችም ተናግሯል፤ 34ጥበቡን ከሰሙት ከዓለም ነገሥታት ሁሉ የተላኩ፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለማድመጥ መጡ።
Currently Selected:
1 ነገሥት 4: NASV
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.