YouVersion Logo
Search Icon

1 ነገሥት 12

12
እስራኤል በሮብዓም ላይ ዐመፀ
12፥1-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 10፥1–11፥4
1እስራኤላውያን ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም መጥተው ስለ ነበር፣ ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ።#12፥1 ወይም በግብጽ ቀረ ተብሎ መተርጐም ይችላል። 2ከንጉሥ ሰሎሞን ሸሽቶ በግብጽ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ሲሰማ፣ ከግብጽ ተመልሶ መጣ። 3እርሱንም ልከው አስጠሩት፤ ከዚያም እርሱና እስራኤል ሁሉ ወደ ሮብዓም መጥተው፣ እንዲህ አሉት፤ 4“አባትህ ቀንበራችንን አከበደብን፤ አንተ ግን አሁን አስጨናቂውን ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር አቅልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት።
5ሮብዓምም፣ “ሂዱ፤ ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ” አላቸው። ስለዚህ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ።
6ከዚያም ንጉሡ ሮብዓም አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ ካገለገሉት ሽማግሌዎች ጋራ ተማከረ፤ “ለዚህ ሕዝብ ምን መልስ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” አላቸው።
7እነርሱም፣ “ዛሬ አንተ ለዚህ ሕዝብ አገልጋይ ብትሆን፣ ብትገዛለትና ደስ የሚያሰኝ መልስ ብትሰጠው፣ ምን ጊዜም አገልጋይህ ይሆናል” ብለው መለሱለት።
8ሮብዓም ግን ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ንቆ፣ ዐብሮ አደጎቹንና በፊቱ ቆመው የሚያገለግሉትን ወጣቶች ምክር ጠየቀ፤ 9እንዲህም አላቸው፤ “ ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚሉኝ ለእነዚህ ሰዎች የምትሰጡኝ ምክር ምንድን ነው? ምንስ ብለን እንመልስላቸው?”
10ዐብሮ አደጎቹም ወጣቶች እንዲህ አሉት፤ “ ‘አባትህ በላያችን ከባድ ቀንበር ጫነብን፣ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚሉህ ለእነዚህ ሰዎች፣ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ይልቅ ትወፍራለች፤ 11አባቴ ከባድ ቀንበር ጫነባችሁ፤ እኔ ግን የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ”
12ንጉሡ፣ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት፣ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም ተመልሰው መጡ። 13ንጉሡም በሽማግሌዎቹ የተሰጠውን ምክር ንቆ ሕዝቡን የሚያስከፋ መልስ ሰጣቸው፤ 14እርሱም ወጣቶቹ በሰጡት ምክር መሠረት፣ “አባቴ ቀንበራችሁን አከበደባችሁ፤ እኔ ደግሞ የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፣ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” አላቸው። 15እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአኪያ አማካይነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ስለ ወሰነ፣ ንጉሡ ሕዝቡን አላዳመጠም።
16መላው እስራኤልም ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤
“ከዳዊት ምን ድርሻ አለን?
ከእሴይስ ልጅ ምን ክፍል አለን?
እስራኤል፣ ሆይ፤ ወደ ድንኳንህ ተመለስ፤
ዳዊት ሆይ፤ አንተም የገዛ ቤትህን ጠብቅ።”
ስለዚህ እስራኤላውያን ወደ የቤታቸው ተመለሱ። 17ይሁን እንጂ ሮብዓምም በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ ነገሠ።
18ንጉሥ ሮብዓም የጕልበት ሠራተኞች አለቃ የነበረውን አዶኒራምን#12፥18 አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ቅጆችና የሱርስት ትርጕሞች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ (1ነገ 4፥6፤ 5፥14 ይመ) ዕብራይስጡ፣ አዶራም ይላል። ላከው፤ ነገር ግን እስራኤል ሁሉ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሡ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ። 19ስለዚህ እስራኤል እስከ ዛሬ ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንዳመፀ ነው።
20ኢዮርብዓም መመለሱን እስራኤላውያን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ ወደ ጉባኤያቸው በማስጠራት በመላው እስራኤል ላይ አነገሡት። ለዳዊት ቤት በታማኝነት ጸንቶ የተገኘው የይሁዳ ቤት ብቻ ነው።
21ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፣ የእስራኤልን ቤት ወግተው መንግሥቱን ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲመልሱ መላውን የይሁዳ ቤትና የብንያምን ነገድ ሰበሰበ፤ የሰራዊቱም ቍጥር አንድ መቶ ሰማንያ ሺሕ ነበር።
22ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ሆነው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ፤ 23“ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፣ ለመላው ይሁዳና ብንያም፣ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ በል፤ 24እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ይህ ነገር ከእኔ የሆነ ነውና ወንድሞቻችሁን እስራኤላውያንን ለመውጋት አትውጡ፤ እያንዳንዳችሁ ወደየቤታችሁ ተመለሱ።’ ” ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ፤ ወደየቤታቸውም ተመለሱ።
በቤቴልና በዳን የቆሙ የወርቅ ጥጆች
25ከዚያም ኢዮርብዓም በኰረብታው አገር በኤፍሬም የምትገኘውን ሴኬምን ምሽግ አድርጎ ሠራ፤ በዚያም ተቀመጠ። ደግሞም ያን ትቶ በመውጣት የጵኒኤልን ምሽግ ሠራ።#12፥25 ዕብራይስጡ ጰኑኤል ይለዋል
26ኢዮርብዓም በልቡ እንዲህ ሲል ዐሰበ፤ “መንግሥቱ ለዳዊት ቤት የሚመለስ ይመስላል፤ 27ይህ ሕዝብ መሥዋዕት ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚወጣ ከሆነ፣ እንደ ገና ልቡን ወደ ጌታው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ሊያዞር ነው። ከዚያም እኔን ይገድለኛል፤ ወደ ንጉሡም ወደ ሮብዓም ይመለሳል።”
28ንጉሡ ከመከረበት በኋላ ሁለት የወርቅ ጥጆች አሠርቶ ሕዝቡን፣ “እስራኤል ሆይ፤ ወደ ኢየሩሳሌም እስካሁን የወጣኸው ይበቃል፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው” አለ። 29አንዱን በቤቴል ሌላውንም በዳን አቆመው። 30ይህም አድራጎት ኀጢአት ሆነ፤ ሕዝቡም በዚያ ላለው ለመስገድ እስከ ዳን ድረስ ርቆ ሄደ።
31ኢዮርብዓም በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ አብያተ ጣዖታትን ሠራ፤ ከሕዝቡ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ፣ ሌዋውያን ካልሆኑት ካህናትን ሾመ። 32በይሁዳ እንደሚደረገው ሁሉ ኢዮርብዓምም በስምንተኛው ወር ዐሥራ ዐምስተኛው ቀን በዓል እንዲሆን ወሰነ፤ በመሠዊያውም ላይ መሥዋዕት አቀረበ። ለሠራቸው ጥጆች መሥዋዕት በማቅረብም እንዲህ ያለውን ድርጊት በቤቴል ፈጸመ። በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ ላሠራቸው አብያተ ጣዖታት በቤቴል ካህናቱን መደበ። 33ራሱ በመረጠው በስምንተኛው ወር፣ በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን በቤቴል ባቆመው መሠዊያ ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ ስለዚህ ለእስራኤላውያን በዓል ወሰነላቸው፤ ዕጣንም ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጣ።

Currently Selected:

1 ነገሥት 12: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in