YouVersion Logo
Search Icon

1 ቆሮንቶስ 6

6
መካሰስ በክርስቲያኖች መካከል
1ከመካከላችሁ አንድ ሰው ከሌላው ጋር ሙግት ቢኖረው፣ ጕዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፈንታ እንዴት ደፍሮ በማያምኑ ሰዎች ፊት ለመፋረድ ያቀርባል? 2ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ እንግዲያው፣ በትንሹ ነገር ላይ ለመፍረድ አትበቁምን? 3በምድራዊ ሕይወት ጕዳይ ቀርቶ፣ በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? 4እንግዲህ እንዲህ ያለ ጕዳይ ሲያጋጥማችሁ፣ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጅ አድርጋችሁ ሹሟ#6፥4 ወይም በቤተ ክርስቲያን የተናቁ ሰዎችን ፈራጅ አድርጋችሁ ትሾማላችሁ?! 5ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ብዬ ነው። ለመሆኑ ከመካከላችሁ ወንድሞችን ለማስታረቅ የሚበቃ አስተዋይ ሰው የለምን? 6ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ለመክሰስ ፍርድ ቤት ይሄዳል፤ ያውም በማያምኑ ሰዎች ፊት!
7እንግዲህ በመካከላችሁ መካሰስ መኖሩ ራሱ ውድቀታችሁን ያሳያል። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? 8እናንተ ግን ራሳችሁ ትበድላላችሁ፤ ታታልላላችሁም፤ ያውም እኮ ወንድሞቻችሁን።
9ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ 10ወይም ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። 11ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል።
የዝሙት ኀጢአት
12“ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ምንም ነገር በእኔ ላይ አይሠለጥንም። 13ደግሞም፣ “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤” እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው። 14እግዚአብሔር ጌታን ከሙታን እንዳስነሣው፣ እኛንም ደግሞ በኀይሉ ከሙታን ያስነሣናል። 15ሰውነታችሁ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? ታዲያ፣ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ ከዝሙት ዐዳሪ ሴት ብልቶች ጋር አንድ ላድርገውን? ከቶ አይገባም! 16ወይስ ከዝሙት ዐዳሪ ጋር የሚተባበር ሰው ከእርሷ ጋር አንድ ሥጋ እንደሚሆን አታውቁምን? “ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ተብሏልና። 17ነገር ግን ከጌታ ጋር የሚተባበር ከእርሱ ጋር አንድ መንፈስ ይሆናል።
18ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚሠራው ኀጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚፈጽም ግን በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል። 19ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ 20በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።

Currently Selected:

1 ቆሮንቶስ 6: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy