YouVersion Logo
Search Icon

1 ቆሮንቶስ 16

16
ለቅዱሳን የተደረገ የገንዘብ መዋጮ
1አሁን ደግሞ ለቅዱሳን ስለሚደረገው ገንዘብ ማሰባሰብ፤ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት አድርጉ። 2ገንዘብ ማሰባሰብ የሚደረገው እኔ በምመጣበት ጊዜ እንዳይሆን፣ ከእናንተ እያንዳንዱ እንደ ገቢው መጠን በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እየለየ ያስቀምጥ። 3በምመጣበት ጊዜ እናንተ ለመረጣችኋቸው ሰዎች የመሸኛ ደብዳቤ ሰጥቼ ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ። 4የእኔ መሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ አብረውኝ ይሄዳሉ።
የሐዋርያው ዕቅድ
5በመቄዶንያ በኩል ማለፌ ስለማይቀር፣ መቄዶንያ ከደረስሁ በኋላ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 6ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጕዞዬ እንድትረዱኝ፣ እናንተ ዘንድ እቈይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር እሰነብት ይሆናል። 7አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ ጌታ ቢፈቅድ ረዘም ላለ ጊዜ እናንተ ዘንድ ለመሰንበት ተስፋ አደርጋለሁ። 8ነገር ግን እስከ በዓለ አምሳ በኤፌሶን እቈያለሁ፤ 9ምክንያቱም ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤ ብዙ ተቃዋሚዎችም አሉብኝ።
10ጢሞቴዎስ ወደ እናንተ ከመጣ፣ አብሯችሁ ያለ ፍርሀት እንዲቀመጥ አድርጉ፤ እርሱም እንደ እኔ የጌታን ሥራ የሚሠራ ነውና። 11ስለዚህ ማንም አይናቀው፤ በሰላም ወደ እኔ እንዲመለስ ርዱት፤ መመለሱንም ከወንድሞች ጋር እየጠበቅን ነው።
12ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ደግሞ፣ ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ አጥብቄ ለምኜው ነበር፤ እርሱ ግን አሁን ለመምጣት አልፈለገም፤ ሲመቸው ግን ይመጣል።
13ንቁ፤ በእምነት ጽኑ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ፤ 14የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ።
15የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች በአካይያ የመጀመሪያዎቹ አማኞች እንደ ሆኑና ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ። ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እለምናችኋለሁ፤ 16እንደ እነርሱ ላሉትና ከእነርሱም ጋር በአገልግሎት ለሚደክሙ ሁሉ ታዘዙ።
17እስጢፋኖስ፣ ፈርዶናጥስና አካይቆስ በመምጣታቸው ደስ ብሎኛል፤ ምክንያቱም እናንተ እዚህ ባለመኖራችሁ የጐደለኝን አሟልተዋል፤ 18የእኔንም የእናንተንም መንፈስ አሳርፈዋልና። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች መታወቅ ይገባቸዋል።
የመሰናበቻ ቃል
19በእስያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
አቂላና ጵርስቅላ#16፥19 በግሪኩ ጵርስቃየጵርስቅላ ሌላው አጠራር ነው።፣ በቤታቸውም ያለችው ቤተ ክርስቲያን የከበረ ሰላምታ በጌታ ያቀርቡላችኋል።
20ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ።
21ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ የጻፍሁላችሁ እኔ ጳውሎስ ነኝ።
22ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታ ሆይ፤ ና!#16፥22 በአራማይክ ጌታ ሆይ፤ ና ማለት ማራናታ ማለት ነው።
23የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
24ፍቅሬ በክርስቶስ ኢየሱስ ከሁላችሁ ጋር ነው፤ አሜን።#16፥24 አንዳንድ ቅጆች አሜን የሚለው የላቸውም።

Currently Selected:

1 ቆሮንቶስ 16: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy