YouVersion Logo
Search Icon

1 ቆሮንቶስ 11

11
1እኔ የክርስቶስን ምሳሌ እንደምከተል እናንተም የእኔን ተከተሉ።
ሥርዐት ያለው አምልኮ
2በሁሉም ነገር ስለምታስቡልኝና ከእኔ የተቀበላችሁትን ትምህርት#11፥2 ወይም ወግ አጥብቃችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።
3ነገር ግን ይህን እንድታውቁ እወድዳለሁ፤ የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው። 4ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ወንድ የእርሱን ራስ ያዋርዳል፤ 5ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ማንኛዋም ሴት የእርሷን ራስ ታዋርዳለች፤ ጠጕሯን እንደ ተላጨች ይቈጠራልና። 6ሴት ራሷን የማትሸፍን ከሆነ፣ ጠጕሯን ትቈረጥ፤ ጠጕሯን መቈረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር መስሎ ከታያት ግን ራሷን ትሸፈን።
7ወንድ ራሱን መከናነብ የለበትም፤#11፥4-7 ወይም የራሱን ጠጕር አስረዝሞ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ወንድ ራሱ የሆነውን ያዋርዳል፤ 5 ራሷን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ማንኛዋም ሴት ራሷ የሆነውን ታዋርዳለች፤ እንዲህ ያለችው ሴት ጠጕራቸውን ከተላጩ ሴቶች አንዷን ትመስላለችና። ሴት ራሷን የማትከናነብ ከሆነ፣ ጠጕሯን ታሳጥር፤ ጠጕሯን መቈረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ስለሆነ ግን እንደ ገና ታሳድገው። 7 ወንድ ጠጕሩን ማስረዘም የለበትም፤ ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ነውና፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት፤ 8ምክንያቱም ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ ከሴት አልተገኘም። 9ደግሞም ሴት ለወንድ ተፈጠረች እንጂ ወንድ ለሴት አልተፈጠረም። 10በዚህ ምክንያት፣ በመላእክትም ምክንያት፣ ሴት በሥልጣን ሥር መሆኗን የሚያሳይ ምልክት በራሷ ላይ ታድርግ።
11በጌታ ዘንድ ግን ሴት ያለ ወንድ፣ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም። 12ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች ሁሉ፣ ወንድም ከሴት ይወለዳልና፤ ነገር ግን የሁሉም መገኛ እግዚአብሔር ነው።
13እስቲ እናንተ ፍረዱ፤ ሴት ራሷን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይገባታልን? 14ወንድ ጠጕሩን ቢያስረዝም ነውር እንደሚሆንበት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን? 15ሴት ግን ጠጕሯን ብታስረዝም ክብሯ አይደለምን? ረዥም ጠጕር የተሰጣት መጐናጸፊያ እንዲሆናት ነውና። 16እንግዲህ ማንም በዚህ ጕዳይ ላይ መከራከር ቢፈልግ፣ እኛም ሆንን የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ከዚህ የተለየ ልማድ የለንም።
የጌታ እራት
11፥23-25 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥26-28ማር 14፥22-24ሉቃ 22፥17-20
17ነገር ግን በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለሚጐዳ እንጂ ለሚጠቅም ስላልሆነ፣ ይህን ትእዛዝ ስሰጥ እያመሰገንኋችሁ አይደለም። 18ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ ሰምቻለሁ፤ ይህም ሊሆን እንደሚችል በከፊል አምናለሁ። 19ከእናንተ መካከል እውነተኞቹ ተለይተው ይታወቁ ዘንድ፣ ይህ መለያየት በመካከላችሁ መኖሩ የግድ ነው። 20በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉት የጌታን እራት አይደለም፤ 21በምትበሉበት ጊዜ አንዱ ሌላውን ሳይጠብቅ ምግቡን ይበላልና፤ አንዱ እየተራበ ሌላው ይሰክራል። 22ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በመናቅ፣ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ፈጽሞ አላመሰግናችሁም።
23እኔ ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ ዐልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንጀራን አንሥቶ 24ከባረከ በኋላ ቈርሶ፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬም አድርጉት” አለ። 25እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ ስለዚህ ከጽዋው በምትጠጡበት ጊዜ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። 26ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።
27እንግዲህ ማንም ሳይገባው፣ ይህን እንጀራ ቢበላ ወይም የጌታን ጽዋ ቢጠጣ፣ የጌታ ሥጋና ደም ባለ ዕዳ ይሆናል። 28ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ከመብላቱና ከዚህ ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት፣ ራሱን ይመርምር፤ 29ምክንያቱም ማንም የጌታን ሥጋ ሳይገባው#11፥29 ሳይለይ ወይም ሳይገነዘብ ማለት ነው። ቢበላና ቢጠጣ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል፤ ይጠጣልም። 30ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት፣ አንዳንዶችም ያንቀላፉት በዚህ ምክንያት ነው። 31ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብን ነበር። 32ነገር ግን ጌታ በሚፈርድብን ጊዜ እንገሠጻለን፤ ይኸውም ከዓለም ጋር አብረን እንዳንኰነን ነው።
33ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ፤ ለመብላት በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ። 34በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለፍርድ እንዳይሆንባችሁ፣ ማንም የራበው ሰው ቢኖር በቤቱ ይብላ።
ስለ ቀረው ነገር ደግሞ በምመጣበት ጊዜ እደነግጋለሁ።

Currently Selected:

1 ቆሮንቶስ 11: NASV

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy