YouVersion Logo
Search Icon

1 ዜና መዋዕል 29

29
ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የቀረቡ ስጦታዎች
1ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ለመላው ጉባኤ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ወጣትና ልምድም የሌለው ነው። ይህ ታላቅ ሕንጻ የሚሠራው ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር አምላክ በመሆኑ፣ ሥራው ከባድ ነው። 2እኔም ያለኝን ሀብት ለአምላኬ ቤተ መቅደስ ለወርቁ ሥራ ወርቁን፣ ለብሩ ሥራ ብሩን፣ ለናሱ ሥራ ናሱን፣ ለብረቱ ሥራ ብረቱን፣ ለዕንጨቱ ሥራ ዕንጨቱን እንዲሁም ለፈርጥ የሚሆነውን መረግድ፣ ኬልቄዶን#29፥2 የዕብራይስጥ የዚህ ቃል ትርጕም በትክክል አይታወቅም፣ ልዩ ልዩ ኅብር ያላቸውን የከበሩ ድንጋዮች፣ ማናቸውንም ዐይነት የሚያምር ድንጋይና ዕብነበረድ፣ ይህን ሁሉ በብዛት አዘጋጅቻለሁ። 3ከዚህም በቀር ለአምላኬ ቤት ካለኝ ፍቅር የተነሣ፣ ለዚህ ለተቀደሰ ቤት ከዚህ በፊት ከሰጠሁት በተጨማሪ፣ ለዚሁ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የግል ሀብቴ የሆነውን ወርቅና ብር እሰጣለሁ፤ 4ይህም ሦስት ሺሕ መክሊት#29፥4 100 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው የኦፊር ወርቅና ሰባት ሺሕ መክሊት#29፥4 240 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው ንጹሕ ብር ለቤተ መቅደሱ የግድግዳ ግንብ ማስጌጫ 5እንዲሁም ለወርቁ ሥራ፣ ለብሩ ሥራ፣ በባለሙያዎች ለሚሠራው ሥራ ሁሉ የሚሆን ነው። ታዲያ ዛሬ ራሱን ለእግዚአብሔር ለመቀደስ ፈቃደኛ የሚሆን ማን ነው?”
6ከዚያም የቤተ ሰብ መሪዎች፣ የነገዱ የእስራኤል ሹማምት፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም በንጉሡ ሥራ ላይ የተመደቡ ሹማምት በፈቃዳቸው ሰጡ፤ 7ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ የሰጡትም አምስት ሺሕ መክሊት#29፥7 170 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው ወርቅ፣ ዐሥር ሺሕ ዳሪክ#29፥7 84 ኪሎ ግራም ያህል ነው ወርቅ፣ ዐሥር ሺሕ መክሊት#29፥7 345 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው ብር፣ ዐሥራ ስምንት ሺሕ መክሊት#29፥7 610 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው ናስ አንድ መቶ ሺሕ መክሊት#29፥7 345 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው ብረት ነው። 8የከበሩ ድንጋዮች ያለውም ሁሉ፣ በጌድሶናዊው በይሒኤል አማካይነት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አስገባ። 9ስጦታው በገዛ ፈቃድና በፍጹም ልብ የቀረበ በመሆኑ፣ አለቆቹ ስላደረጉት የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሕዝቡ ደስ አለው፤ ንጉሥ ዳዊትም እንደዚሁ እጅግ ደስ አለው።
የዳዊት ጸሎት
10ዳዊትም በመላው ጉባኤ ፊት እግዚአብሔርን እንዲህ ሲል አመሰገነ፤
“የአባታችን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤
ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአንተ ምስጋና ይሁን።
11 እግዚአብሔር ሆይ፤ በሰማይና
በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና፤
ታላቅነት፣ ኀይል፣ ክብርና ግርማ የአንተ ነው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ መንግሥትም የአንተ ነው፤
አንተም እንደ ራስ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያልህ ነህ።
12ባለጠግነትና ክብር የሚገኘው ከአንተ ነው፤
አንተም የሁሉ ገዥ ነህ፤
ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለሁሉም ብርታትን ለመስጠት፣
ብርታትና ኀይል በእጅህ ነው።
13አምላካችን ሆይ፤ አሁንም እናመሰግንሃለን፤
ለከበረው ስምህም ውዳሴ እናቀርባለን።
14“ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፤ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ቸርነት እናደርግ ዘንድ እኔ ማነኝ? ሕዝቤስ ማነው? 15እኛም እንደ ቀድሞ አባቶቻችን በፊትህ መጻተኞችና እንግዶች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው፤ ተስፋ ቢስም ነው። 16እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ለተቀደሰው ስምህ ቤተ መቅደስ እንሠራልህ ዘንድ ይህ በብዛት ያዘጋጀነው ሁሉ፣ ከእጅህ የተገኘና ሁሉም የአንተ ነው። 17አምላኬ ሆይ፤ ልብን እንደምትመረምርና ቅንነትን እንደምትወድድ ዐውቃለሁ፤ እኔም ይህን ሁሉ የሰጠሁት በበጎ ፈቃድና በቀና መንፈስ ነው። አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በበጎ ፈቃዱ እንዴት እንደ ሰጠ አይቻለሁ። 18የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህን ሐሳብ ለዘላለም በሕዝብህ ልብ ጠብቀው፤ ልባቸውንም ለአንተ ታማኝ አድርገው። 19ትእዛዞችህን፣ ደንብህንና ሥርዐትህን እንዲጠብቅ፣ እኔ ባዘጋጀሁለት ነገሮች ታላቅ ሕንጻ ለመሥራት እንዲችል፣ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ፈቃደኝነት ስጠው።”
20ከዚያም ዳዊት ለመላው ጉባኤ፣ “አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱት” አላቸው። ስለዚህ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ወደሱ፤ በእግዚአብሔር በንጉሡም ፊት ተደፍተው ሰገዱ።
ሰሎሞን ንጉሥ መሆኑ በይፋ ታወቀ
29፥21-25 ተጓ ምብ – 1ነገ 1፥28-53
21በማግስቱም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሠዉ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም አቀረቡ፤ ይህም አንድ ሺሕ ወይፈን፣ አንድ ሺሕ አውራ በግ፣ አንድ ሺሕ የበግ ጠቦት ሲሆን፣ ከመጠጥ ቍርባኖቻቸውና ከሌሎች መሥዋዕቶች ጋር ስለ እስራኤል ሁሉ በብዛት አቀረቡ። 22በዚያችም ዕለት በእግዚአብሔር ፊት በታላቅ ደስታ በሉ፤ ጠጡም።
ከዚያም የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ንጉሥ መሆኑን ለሁለተኛ ጊዜ በይፋ ዐወቁ፤ ገዥ እንዲሆንም በእግዚአብሔር ፊት ቀቡት፤ ሳዶቅንም ካህናቸው እንዲሆን ቀቡት። 23ሰሎሞንም ነግሦ በአባቱ በዳዊት ምትክ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ ተከናወነለት፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት። 24የጦር አለቆቹና ኀያላኑ ሁሉ እንዲሁም የንጉሡ የዳዊት ወንዶች ልጆች በሙሉ ታማኝነታቸውን ለንጉሥ ሰሎሞን አረጋገጡለት።
25 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ ሁሉ እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከእርሱ በፊት ለነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ያላጐናጸፋቸውን ንጉሣዊ ክብር ሁሉ ሰጠው።
የዳዊት መሞት
29፥26-28 ተጓ ምብ – 1ነገ 2፥10-12
26የእሴይ ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር። 27እርሱም በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት፣ በአጠቃላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 28ብዙ ዘመን ባለጠግነትና ክብር ሳይጐድልበት ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ልጁ ሰሎሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
29በንጉሥ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከናወነው ድርጊት በባለ ራእዩ በሳሙኤል የታሪክ መጽሐፍ፣ በነቢዩ በናታን የታሪክ መጽሐፍ፣ በባለ ራእዩ በጋድ የታሪክ መጽሐፍ ተጽፏል። 30የተጻፈውም በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ከፈጸማቸው ዝርዝር ጕዳዮችና በዙሪያው ከከበቡት፣ ከእስራኤልና ከሌሎች አገር መንግሥታት ታሪክ ጋር ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy