YouVersion Logo
Search Icon

ትን​ቢተ ሚል​ክ​ያስ 2

2
1አሁንም እናንተ ካህናት ሆይ፥ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።
2ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድዳባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ፣ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ።
3እነሆ፥ ክንዳችሁን እገሥጻለሁ፥ የመሥዋዕታችሁንም ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፣ ከእርሱም ጋር በአንድነት ትወሰዳላችሁ።
4ቃል ኪዳኔ ከሌዊ ጋር ይሆን ዘንድ ይህን ትእዛዝ እንደ ሰደድሁላችሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
5ቃል ኪዳኔ ከእርሱ ጋር የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነበረ፣ ይፈራ ዘንድም እነርሱን ሰጠሁት፣ እርሱም ፈራኝ፥ ከስሜም የተነሣ ደነገጠ።
6የእውነት ሕግ በአፉ ውስጥ ነበረች፥ በከንፈሩም ውስጥ በደል አልተገኘበትም፣ ከእኔም ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፥ ብዙ ሰዎችንም ከኃጢአት መለሰ።
7ካህኑ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ከንፈሮቹ እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ይገባቸዋል፥ ሰዎችም ሕግን ከአፉ ይፈልጉ ዘንድ ይገባቸዋል።
8እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል፣ በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፣ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
9ስለዚህ መንገዴን እንዳልጠበቃችሁ፥ በሕግም ለሰው ፊት እንዳዳላችሁ መጠን፥ እኔ ደግሞ በሕዝብ ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ አድርጌአችኋለሁ።
10ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን? የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን ለማስነቀፍ እኛ እያንዳዳችን ወንድማችንን ስለ ምን አታለልን?
11እግዚአብሔር የወደደውን መቅደስ ይሁዳ አርክሶአልና፥ የእንግዳውንም አምላክ ልጅ ሚስት አድርጎ አግብቶአልና ይሁዳ አታልሎአል፥ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ውስጥ ርኵሰት ተሠርቶአል።
12ይህን ከሚያደርግ ሰው፥ እግዚአብሔር የሚጠራውንና የሚመልሰውን ለሠራዊትም ጌታ ለእግዚአብሔር ቍርባን የሚያቀርበውን ከያዕቆብ ድንኳን ያጠፋል።
13ይህንም ደግሞ አድርጋችኋል፣ እግዚአብሔር ቍርባኑን ዳግመኛ እንዳይመለከት፥ ከእጃችሁም በደስታ እንዳይቀበለው መሠዊያውን በእንባና በልቅሶ በኅዘንም ትከድናላችሁ።
14እናንተም፦ ስለ ምንድር ነው? ብላችኋል። ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው።
15እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድር ነው? ዘር አይደለምን? ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፥ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል።
16መፋታትን እጠላለሁ፥ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፥ ልብሱንም በግፍ ሥራ የሚከድነውን ሰው እጠላለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ስለዚህ እንዳታታልሉ መንፈሳችሁን ጠብቁ።
17እግዚአብሔርን በቃላችሁ አታክታችኋል። እናንተም፦ ያታከትነው በምንድር ነው? ብላችኋል። ክፉን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ መልካም ነው፥ እርሱም በእነርሱ ደስ ይለዋል፣ ወይስ፦ የፍርድ አምላክ ወዴት አለ? በማለታችሁ ነው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy