መጽሐፈ ሲራክ 41
41
ሞት
1ሞት ሆይ! ንብረቱን እንደ ያዘ በሰላም ለሚኖር፥ ያለአንዳች ጭንቀት ኑሮውን ለሚመራና በምግብም ለሚደሰት ሰው አንተን ማሰብ ምንኛ ያሰቅቃል! 2ሞት ሆይ! ኃይሉ ለደከመበትና ችግር ላጐሳቆለው፥ እርጅና ለተጫነውና የሺህ ጭንቀቶች ጐሬ ለሆነው፥ ለቁጡውና ትዕግሥት ላጣው ፍርድህ አስደሳች ነው። 3የሞትን ፍርድ አትፍሩ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን፥ ከኋላችሁም የሚመጡትን አስቡ። 4ለፍጡራን ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ይህ ነው፤ መልካም የሆነውን እርሱ ያውቃልና። ስለምን የእርሱን ፈቃድ እንቃወማለን? ለዓሥር፥ ለመቶ ወይም ለሺህ ዓመታት በሕይወት ብትኖር ዕድሜህን በሲኦል ውስጥ አትጠየቅበትም። 5የኃጢአተኞች ልጆችን የመሰሉ ያልተባረኩ ዘሮች፥ በክፉዎች መናፍስት ጥላ ሥር ይሰበሰባሉ። 6የክፉዎች ልጆች ውርስ ዕጣው ጥፋት ነው፤ ዘራቸውም ውርደትን ተከናንቦ ይኖራል። 7ክፉ አባት በልጆቹ ላይ ላመጣው ውርደት፥ በእነርሱው አንደበት ይወቀሳል። 8የልዑል እግዚአብሔርን ሕግ የጣሳችሁ፥ እናንት ኃጢአተኞች፥ የተከተላችሁት መንገድ አያዘልቃችሁም። 9የተወለዳችሁት ለእርግማን፥ በሞታችሁም ጊዜ ድርሻችሁ እርግማን ነው። 10ከመሬት የተገኘ ሁሉ፥ ወደ እርሷ ይመለሳል፤ ክፉዎችም እንዲሁ ከእርግማን ወደ ጥፋት ያመራሉ። 11የሚታዘነው ለሙታን በድን ብቻ ነው፤ ዋጋ ቢስ የኃጥአን ስም ግን ይጠፋል። 12ስለ ክብርህ ተጠንቀቅ፤ ከሺህ የወርቅ ክምር የበለጠ ይኖርሃልና። 13ጥሩ ሕይወት እድሜው አጭር ነው። መልካም ስም ግን ለዘለዓለም ይኖራል።
ኃፍረት
14ልጆቼ ሆይ! ትእዛዞቼን ጠብቁ፥ በሰላምም ኑሩ፥ የተደበቀ ጥበብና የማይሰሩበት ሃብት፥ ከቶ ምን ይጠቅማል? 15ጥበብን ከሚደብቅ ሰው ይልቅ፥ ሞኝነቱን የሚደብቅ ይሻላል። 16በሁሉም ነገር ማፈር አይገባም፤ ሁሉም ነገር ከሁሉም ሰው ትክክለኛ ግምትን አያገኝም፤ በሚከተሉት ሁኔታዎች ግን ኃፍረት ይሰማህ። 17በእናትህና በአባትህ ፊት ያልተገባ ፀባይ ስታሳይ፥ በመሪዎችና በልዑላን ፊት ውሸት ስትናገር፥ 18በዳኛው ወይም በሕግ ባለ ሥልጣን ፊት ስትበድል፥ በሕዝብ ጉባኤ ፊት ስታጠፋ፥ 19በጓደኞችህና በወዳጆችህ ፊት ስትወሰልት፥ በጐረቤቶችህም ፊት ስትሰርቅ፥ እፍረት ይሰማህ። 20በእውነትና በእግዚአብሐር ቃል ኪዳን ፊት፥ በመሠዊያው ላይ በመደገፍህ፥ 21ስትሰጥም ሆነ ስትቀበል ትሕትና ባለማሳየትህ፥ ሰላምታ ላቀረቡልህ ሰላምታ በመንፈግህ፥ 22ጋለሞታዋን ትኩር ብለህ በማየትህ፥ ወገንህን በመግፋትህ፥ 23የሌላውን ድርሻ ወይም ስጦታ የግልህ በማድረግህ፥ የሌላውን ሰው ሚስት በማሽኮርመምህ፥ 24ሴት አገልጋዩን በመመኘትህ፥ ወደ አልጋዋ አትጠጋ 25ወደጆችህን በማስቀየምህ ከስጦታ በኋላ አትሳለቅ፤ 26የሰማውን ሁሉ በመናገርህ፥ ምሥጢሮችን በማውጣትህ፥ እፍረት ይሰማህ። 27የኔ እውነተኛ ኀፍረት ምን እንደሆነ ታውቃለህ፤ በሁሉም ሰው ዘንድም ትከበራለህ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 41: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in