መጽሐፈ ሲራክ 38
38
ሕክምናና በሽታ
1አገልግሎቱን በማየት የእግዚአብሔርም ፍጡር በመሆኑ፥ ሐኪሙን በሚገባ አክብረው። 2ከንጉሥ እንደሚቀበሉት ስጦታ ፈውስ የሚገኘውም ከታላቁ ልዑል እግዚአብሔር ነው። 3የሐኪሙ እውቀት ያኮራዋል፤ ታላላቅ ሰዎችም ያከብሩታል። 4እግዚአብሔር ፈውስ የሚሆኑ ሥራ ሥሮችን ከመሬት አፈራ፤ አዋቂ ሰውም አይንቃቸውም። 5#ዘፀ. 15፥23-25።የእንጨት ቁራጭ ኃይሉን ለማሳየት፥ ውሃውን ጣፋጭ አላደረገምን? 6ከታላላቅ ሥራዎቹ ይጠቀሙ ዘንድ፥ ለአንዳንድ ሕዝቦች እግዚአብሔር ዕውቀትን ሰጥቷል። 7ሥራ ሥሮች ፈውስ ይሆናሉ፤ ሕመምንም ያስታግሳሉ፤ ሐኪሙም ይቀምማቸዋል። 8ለእግዚአብሔር ሥራ ፍጻሜ የለውም፤ ለእርሱ ምስጋና ይግባውና ጤንነት በዓለም ሰፍኗል። 9ልጄ ሆይ! በታመምህ ጊዜ ዐመፀኛ አትሁን፤ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፤ እርሱም ያድንሃል። 10ከበደል ራቅ፤ እጆችንም አታሳድፍ፤ ልብህንም ከኃጢአት ሁሉ አንጻ። 11ዕጣንንና የመታሰቢያ ዱቄት ስጥ፤ አቅምህ የፈቀደውን የተሻለ መሥዋዕት አቅርብ። 12ከዚህ በኋላ ወደ ሐኪም ሂድ፤ እርሱንም የፈጠረው እግዚአብሔር ነውና። ያስፈልግሃልና ካንተ አይራቅ። 13መልካም ጤንነት በሀኪሞች ብርታት የሚወሰንበት ወቅት አለ። 14እነርሱም በተራቸው ፈውስን ይሰጡ ዘንድ፥ ያድኑ፥ ዕድሜንም ይቀጥሉ ዘንድ፥ እግዚአብሔር የማዳን ሞገስን ይሰጣቸው ዘንድ፥ ይጸልያሉና። 15በፈጣሪው ፊት ኃጢአት የሚሠራ፥ በሐኪም እጅ ይውደቅ!
ኀዘን
16 #
ሲራ. 22፥11፤12። ልጄ ሆይ! ስለ ሞተ ሰው አልቅስ፤ ኀዘንህንም በእንጉርጉሮ አሰማ፤ በተገቢው ሥርዓት አስክሬንን ቅበር፤ መቃብሩንም አክብር። 17አምርረህ አንባ፤ ደረትህን ድቃ፤ ከሰው ሐሜት እንድትድን፥ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን፥ ለሟች የሚገባውን ኀዘን አድርግ። ከዚህ በኋላ ግን ተጽናና። 18መሪር ኀዘን ሞትን ያመጣል፤ ሰቆቃ የበዛበት ልብም ትደክማለችና። 19በመከራ ጊዜ ኀዘን ይጸናል፤ የስቃይ ሕይወት ሸክሙ ይከብዳል። 20ልብህን በኀዘን አታሰቃይ፤ ገለል አድርገው፤ ፍጻሜህን አስብ። 21መመለስ እንደሌለ አትዘንጋ፤ ሟቹን ማዳን አትችልም፤ ራስህንም ትጐዳለህ። 22ዕጣዬን አስታውስ፤ ያንተም ዕጣ ይኸው ነውና፥ እኔ ትናንት አንተ ደግሞ ዛሬ! 23ሙታን አንዴ ካረፉ፥ መታሰቢያውም እንዲሁ ይሁን፤ መንፈሳቸው ከራቀ በኋላ ስለ እነርሱ አትዘን።
የተለያዩ ሙያዎችና የእጅ ጥበብ
24ጸሐፊው በትርፍ ጊዜው ጥበብን ይቀስማል፤ በሥራ ይልተጠመደ ሰው ጥበበኛ ሊሆን ይችላል። 25እርፍ የሚጨብጥ፥ ፎላጐቱ በዘንጉ መጠቀም የሆነ፥ በሥራ የተጠመዱትን በሬዎች የሚነዳ፥ 26ስለ ቀደዳቸው ፈሮች ብዙ የሚያስብ፥ ሌቱን ጊደሮቹን ለማደለብ የሚተጋ፥ ገበሬ እንደምን ጥበበኛ ይሆናል? 27ሠራተኞችና የእጅ ባለሙያዎችም፥ ቀን ከሌት ይደክማሉና እንዲሁ ናቸው። ማኀተሞች የሚቀርጹ፥ አዳዲስ ንድፋቸውንም መልሰው የሚቀርጹ፥ ሥራቸውንም ለማጠናቀቅ ሌትም የሚሠሩ፤ ባተሌዎች በመሆናቸው ጥበብን ለመቅሰም ጊዜ አይኖራቸውም። 28ከመስፉ አጠገብ የሚቀመጠውም አንጥረኛ እንዲሁ ነው። ከብረቱ ምን እንደሚቀርጽ ያስባል፥ የእሳቱ ወላፈን ቆዳውን ይለበልበዋል፥ ከወናፉ ሙቀትም ጋር ይታገላል፥ የመዶሻው ድምፅ ያደነቁረዋል፥ ዐይኖቹም በሚያወጣቸው ቅርጾች ላይ ተተክለዋል፥ ቀልቡን በሥራው ላይ ያሳርፋል፥ ሥራውንም በሚገባ ካላጠናቀቀ ቢመሽ እንኳ አያርፍም። 29ሥራውን በትጋት የሚሠራውም ሸክላ ሰሪ እንዲሁ ነው፤ መንኮራኮሩን በእግሩ ያሸከረክራል፥ ያለማቋረጥ ሥራውን ይከታተላል፥ እያንዳንዷ የጣት እንቅስቃሴ የተጠናች ነች። 30ጭቃውን በክንዱ ይጠፈጥፈዋል፥ በእግሩ ያባካዋል፥ በሚገባም ይለቀልቀዋል፥ ማድረቂያውንም ሲያጸዳ ያመሻል። 31እኒህ ሰዎች ሁሉ በእጆቻቸው ይተማመናሉ፤ እያንዳንዱም በየሙያው አዋቂ ነው። 32አንዲት ከተማ ያለእነርሱ ሰው ሊኖርባት አይችልም፤ በዚያም ሰፈር ማድረግ፥ መጓዝም አይቻልም። 33በምክር ቤቱ ውስጥ ግን እነርሱን አታገኛቸውም፤ በጉባኤውም ውስጥ ሥልጣን የላቸውም፤ በዳኝነት ወንበር ላይ አይቀመጡም፤ የሕጉን አሠራርም አያውቁም፤ 34ባህላቸው ወይም ፍርዳቸው የሚመረጥ አይደለም፤ ከፈላስፎችም ዘንድ አዘውትረው አይቀርቡም፤ የምድርን ወጋግራዎች ይደግፋሉ፤ ጸሎታቸውም ስለ ሥራቸው ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 38: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in