YouVersion Logo
Search Icon

መክብብ 3

3
ለሁሉም ጊዜ አለው
1ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤
ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤
2ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤
ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀልም ጊዜ አለው፤
3ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለማዳንም ጊዜ አለው፤
ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤
4ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤
ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው፤
5ድንጋይ ለመጣል ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤
ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመለያየትም ጊዜ አለው፤
6ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመተው ጊዜ አለው፤
ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤ አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው፤
7ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤
ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው፤
8ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤
ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው።
9ሠራተኛ ከጥረቱ የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው? 10ሰዎች ይደክሙበት ዘንድ አምላክ የሰጣቸውን ከባድ የሥራ ጫና አየሁ። 11ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ አምላክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም። 12ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሠኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። 13ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የአምላክ ችሮታ ነው። 14አምላክ ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ በርሱ ላይ ምንም አይጨመርም፤ ከርሱም ምንም አይቀነስም፤ ሰዎች ይፈሩት ዘንድ ይህን አደረገ።
15አሁን ያለው ከዚህ በፊት የነበረው ነው፤
ወደ ፊት የሚሆነውም ቀድሞ የነበረ ነው፤
አምላክም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል#3፥15 ወይም እግዚአብሔር ያለፈውን መልሶ ይጠራዋል
16ከፀሓይ በታችም ሌላ ነገር አየሁ፤
በፍርድ ቦታ ዐመፅ ነበር፤
በፍትሕ ቦታ ግፍ ነበር።
17እኔም በልቤ፣
“ለማንኛውም ድርጊት፣
ለማንኛውም ተግባር ጊዜ ስላለው፣
አምላክ ጻድቁንና ኀጢአተኛውን ወደ ፍርድ ያመጣቸዋል”
ብዬ አሰብሁ።
18እንዲህም ብዬ አሰብሁ፤ “ሰዎች፣ እንደ እንስሳት መሆናቸውን ያዩ ዘንድ አምላክ ይፈትናቸዋል። 19የሰው ዕድል ፈንታ እንደ እንስሳት ነው፤ ሁለቱም ዕጣ ፈንታቸው አንድ ነው፤ አንዱ እንደሚሞት፣ ሌላውም እንዲሁ ይሞታል። ሁሉ አንድ ዐይነት እስትንፋስ#3፥19 ወይም መንፈስ አላቸው፤ ሰውም ከእንስሳ ብልጫ የለውም፤ ሁሉም ከንቱ ነው። 20ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ፤ ሁሉም ከዐፈር እንደ ሆኑ፣ ተመልሰው ወደ ዐፈር ይሄዳሉ። 21የሰው መንፈስ ወደ ላይ መውጣቱን፣ የእንስሳ እስትንፋስ#3፥21 ወይም የሰው መንፈስ ወደ ላይ እንደሚሄድ ወይም የእንስሳት መንፈስ ደግሞ ወደ ታች ወደ ምድር መውረዱን ማን ያውቃል?”
22ስለዚህ ለሰው ዕጣ ፈንታው ስለ ሆነ፣ በሥራው ከመደሰት የተሻለ ነገር እንደሌለው አየሁ፤ ከርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ተመልሶ እንዲያይ የሚያደርገው ማን ነው?

Currently Selected:

መክብብ 3: NASV

Highlight

Copy

Compare

Share

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in