ኢያሱ 7:1-13

ኢያሱ 7:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ግን እርም በሆ​ነው ነገር ታላቅ በደል በደሉ፤ ከይ​ሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እር​ሱም የከ​ርሚ ልጅ፥ የዘ​ን​በሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ እርም ከሆ​ነው ነገር ወሰደ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ላይ ተቈጣ። ኢያ​ሱም ከቤ​ቴል በም​ሥ​ራቅ በኩል በቤ​ት​አ​ዊን አጠ​ገብ ወዳ​ለ​ችው ወደ ጋይ ሰዎ​ችን ከኢ​ያ​ሪኮ ልኮ፥ “ውጡ፤ ጋይ​ንም ሰልሉ” ብሎ ተና​ገ​ራ​ቸው፤ ሰዎ​ቹም ወጡ፤ ጋይ​ንም ሰለሉ። ወደ ኢያ​ሱም ተመ​ል​ሰው፥ “ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥ​ተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይ​ውጣ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሕዝብ ሁሉ ግን ወደ​ዚያ አት​ው​ሰድ፤ ጥቂ​ቶች ናቸ​ውና” አሉት። ሦስት ሺህ ያህል ሰዎ​ችም ወደ​ዚያ ወጡ፤ የጋ​ይም ሰዎች አባ​ረ​ሩ​አ​ቸው፤ ከፊ​ታ​ቸ​ውም ሸሹ። የጋይ ሰዎ​ችም ከእ​ነ​ርሱ ሠላሳ ስድ​ስት ሰዎ​ችን ገደሉ፤ ከበሩ ጀም​ረው እስከ አጠ​ፉ​አ​ቸው ድረስ አባ​ረ​ሩ​አ​ቸው፤ በቍ​ል​ቍ​ለ​ቱም ገደ​ሉ​አ​ቸው፤ የሕ​ዝ​ቡም ልብ ደነ​ገጠ፤ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያ​ሱም ልብ​ሱን ቀደደ፤ እር​ሱና የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ሽማ​ግ​ሌ​ዎች በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግ​ን​ባ​ራ​ቸው ተደፉ፤ በራ​ሳ​ቸ​ውም ላይ ትቢያ ነሰ​ነሱ። ኢያ​ሱም አለ፥ “ወዮ! ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሆይ! በአ​ሞ​ሬ​ዎ​ና​ው​ያን እጅ አሳ​ል​ፈህ ትሰ​ጠን፥ ታጠ​ፋ​ንም ዘንድ አገ​ል​ጋ​ይህ ይህን ሕዝብ ዮር​ዳ​ኖ​ስን ለምን አሻ​ገረ? በዮ​ር​ዳ​ኖስ ማዶ ተቀ​ም​ጠን በኖ​ርን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ! እስ​ራ​ኤል ጀር​ባ​ውን ወደ ጠላ​ቶቹ ከመ​ለሰ እን​ግ​ዲህ ምን እላ​ለሁ? ከነ​ዓ​ና​ው​ያ​ንም፥ በም​ድ​ሪ​ቱም የሚ​ኖሩ ሁሉ ሰም​ተው ይከ​ብ​ቡ​ናል፤ ከም​ድ​ርም ያጠ​ፉ​ናል፤ ለታ​ላቁ ስም​ህም የም​ታ​ደ​ር​ገው ምን​ድር ነው?” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ኢያ​ሱን አለው፥ “ለምን በግ​ን​ባ​ርህ ተደ​ፍ​ተ​ሃል? ተነሥ! ሕዝቡ በድ​ለ​ዋል፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር የገ​ባ​ሁ​ትን ቃል ኪዳ​ኔን አፍ​ር​ሰ​ዋል፤ እርም ከሆ​ነ​ውም ነገር ሰር​ቀው ወሰዱ፤ በዕ​ቃ​ቸ​ውም ውስጥ ሸሸ​ጉት። ስለ​ዚ​ህም የእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች በጠ​ላ​ቶ​ቻ​ቸው ፊት መቆም አይ​ች​ሉም፤ የተ​ረ​ገሙ ስለ​ሆኑ በጠ​ላ​ቶ​ቻ​ቸው ፊት ይሸ​ሻሉ፤ እርም የሆ​ነ​ው​ንም ነገር ከመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ ካላ​ጠ​ፋ​ችሁ ከዚህ በኋላ ከእ​ና​ንተ ጋር አል​ሆ​ንም። ተነ​ሣና ሕዝ​ቡን ቀድስ እን​ዲ​ህም በላ​ቸው፦ ‘እስ​ራ​ኤል ሆይ! እርም የሆነ ነገር በመ​ካ​ከ​ልህ አለ፤ እር​ምም የሆ​ነ​ውን ነገር ከመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ እስ​ክ​ታ​ጠፉ ድረስ በጠ​ላ​ቶ​ቻ​ችሁ ፊት መቆም አት​ች​ሉም’ ብሎ የእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተና​ግ​ሮ​አ​ልና እስከ ነገ ራሳ​ች​ሁን አንጹ።

ኢያሱ 7:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እስራኤላውያን ግን ዕርም የሆነውን ነገር ለራሳቸው በመውሰድ በደሉ፤ ይህም ከይሁዳ ነገድ የሆነው አካን የከርሚ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የዛራ ልጅ ዕርም ከሆነው ነገር ስለ ወሰደ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱ ከቤቴል በስተምሥራቅ ካለችው ከቤትአዌን አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ጋይ ከኢያሪኮ ሰዎችን ልኮ፣ “ወደዚያ ውጡ፤ አገሪቱንም ሰልሉ” አላቸው፤ ሰዎቹም ወጥተው ጋይን ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው፣ “ጋይን ለመውጋት ሕዝቡ ሁሉ መሄድ አያስፈልገውም፤ በዚያ ያለው ሕዝብ ጥቂት ስለ ሆነ፣ ከተማዪቱን ለመውጋት ሁለት ወይም ሦስት ሺሕ ሰው ስለሚበቃ ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ በመሄድ አይድከም” አሉት። ስለዚህ ሦስት ሺሕ ያህል ሰው ወጣ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሸ፤ የጋይም ሰዎች እስራኤላውያንንም ከከተማዪቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሽባሪም ድረስ በማባረር ቍልቍለቱ ላይ መቷቸው፤ ከእነርሱም ሠላሳ ስድስት ያህል ሰው ገደሉባቸው። ከዚህ የተነሣም የሕዝቡ ልብ ቀለጠ፤ እንደ ውሃም ፈሰሰ። በዚህ ጊዜ ኢያሱ ልብሱን ቀደደ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፋ፤ የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንደዚሁ አደረጉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ አለ፤ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዮርዳኖስን አሻግረህ ይህን ሕዝብ ወደዚህ ያመጣኸው ለአሞራውያን አሳልፈህ በመስጠት እንዲያጠፉን ነውን? ምነው ሳንሻገር እዚያው ማዶ በቀረን ኖሮ! ጌታ ሆይ፤ እስራኤል በጠላቱ ፊት ሲሸሽ እኔ ምን ልበል? ከነዓናውያንና ሌሎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ ይህን ሲሰሙ ይከብቡናል፤ ስማችንንም ከምድር ገጽ ያጠፉታል፤ እንግዲህ ስለ ታላቁ ስምህ ስትል የምታደርገው ምንድን ነው?” እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ለምን በግንባርህ ተደፋህ? እስራኤል በድሏል፤ እንዲጠብቁ ያዘዝኋቸውን ቃል ኪዳኔን ጥሰዋል፤ ዕርም የሆነውን ነገር ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ዋሽተዋል፤ የወሰዱትንም ከራሳቸው ንብረት ጋራ ደባልቀዋል። እንግዲህ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለመቋቋም ያልቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ጀርባቸውን አዙረው የሸሹትም ለጥፋት በመዳረጋቸው ነው። ዕርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ፣ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋራ አልሆንም። “ተነሣ፤ ሕዝቡን ቀድስ፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እስራኤል ሆይ፤ ዕርም የሆነ ነገር በመካከላችሁ ስላለ፣ ይህን ካላስወገዳችሁ ጠላቶቻችሁን ለመቋቋም እንደማትችሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሯልና ለነገ ራሳችሁን ለማዘጋጀት ሰውነታችሁን ቀድሱ።

ኢያሱ 7:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፥ የእግዚአብሔርም ቁጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ልኮ፦ ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ ብሎ ተናገራቸው፥ ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው፦ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፥ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም አሉት። ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፥ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን መቱ፥ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቁልቁለቱም መቱአቸው፥ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም አለ፦ ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ፥ እስራኤል በጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፥ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው? እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፦ ለምን በግምባርህ ተደፍተሃል? ቁም፥ እስራኤል በድሎአል፥ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፥ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፥ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፥ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ እስራኤል ሆይ፥ እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፥ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ተቀደሱ።

ኢያሱ 7:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እስራኤላውያን ግን የተከለከሉ ነገሮችን በተመለከተ ታማኞች ሆነው አልተገኙም፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው ዓካን፥ የከርሚ ልጅ፥ የዘብዲ የልጅ ልጅ፥ የዛራ ልጅ ከተከለከሉት ነገሮች በመውሰድ በእስራኤል ላይ የእግዚአብሔርን ቊጣ አስነሣ። ኢያሱ በኢያሪኮ ሳለ በቤትአዌን አጠገብ ከቤትኤል በስተምሥራቅ የምትገኘውን “ዐይ” ተብላ የምትጠራውን ከተማና የምድሪቱን አቀማመጥ አጥንተው ይመለሱ ዘንድ ጥቂት ሰዎችን ላከ። ይህንንም በትእዛዙ መሠረት ከፈጸሙ በኋላ፥ ለኢያሱ ከዚህ የሚከተለውን ማስረጃ አቀረቡለት፦ “እነርሱ ጥቂቶች ስለ ሆኑ በዐይ ላይ አደጋ ለመጣል ያለውን ሰው ሁሉ በአጠቃላይ ማዝመት አያስፈልግም፤ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ሰዎች ብቻ ላክ፤ በዚያ ለመዋጋት መላውን ሠራዊት አትላክ።” ስለዚህም ሦስት ሺህ እስራኤላውያን ዘምተው አደጋ ጣሉባት፤ ነገር ግን እነርሱ ከዐይ ወታደሮች ፊት ሸሹ፤ የዐይ ሰዎችም ወደ ሠላሳ ስድስት ያኽል ሰዎችን ገደሉባቸው፤ ከከተማይቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሼባሪዎ ቊልቊለት ድረስ እየገደሉ አባረሩአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀልጦ እንደ ውሃ ፈሰሰ። ኢያሱና የእስራኤል መሪዎች በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ ሐዘናቸውን ለመግለጥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ወዮ! እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህን ሕዝብ ለምን ዮርዳኖስን አሻገርከው? አሞራውያን እንዲያጠፉን ለእነርሱ አሳልፈህ ለመስጠት ነውን? ከዮርዳኖስ ማዶ ብንቀመጥ እንዴት በተሻለን ነበር! አምላክ ሆይ፥ እስራኤል ከጠላቶቹ ፊት ከሸሸ እንግዲህ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንና ሌሎችም በዚህች ምድር የሚኖሩት ሁሉ ይህን ነገር ይሰማሉ፤ ስለዚህም ዙሪያችንን ከበው ሁላችንንም ይፈጁናል፤ ታዲያ ስለ ክብርህ የምታደርገው ምንድን ነው?” እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ስለምን በግንባርህ ወደቅኽ? እስራኤላውያን በድለዋል፤ እንዲጠብቁት ያዘዝኳቸውንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ ከተከለከሉት ነገሮች ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ከራሳቸው ንብረት ጋር በማቀላቀል አታላዮች ሆነዋል። እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን መቋቋም ያልቻሉበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ እነርሱ ራሳቸው እንዲጠፉ ስለ ተፈረደባቸው ከጠላቶች ፊት ወደ ኋላ ይሸሻሉ። እንዲደመሰስ የታዘዘውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ሂድ! ሕዝቡን አንጻ! ‘በመካከላችሁ የተከለከለ ነገር ስላለ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለነገ ራሳችሁን አንጹ!’ ይላል በላቸው። እስራኤል ሆይ! ይህን የተከለከለ ነገር ከመካከልህ ካላስወገድህ በጠላቶችህ ፊት ልትቆም አትችልም።

ኢያሱ 7:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ የጌታም ቁጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ላከ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ፤” ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው እንዲህ አሉት፦ “ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፤ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም።” ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን ገደሉ፤ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቁልቁለቱም ላይ ሳሉ መቱአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በጌታ ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ አለ፦ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ልትሰጠን ልታጠፋንም ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ! እስራኤል ከጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ እንግዲህ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድነው?” ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ለምን በግምባርህ ተደፍተኽ ትሰግዳለህ? ቁም፤ እስራኤል ኃጢአት ሠርቶአል፤ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፤ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ ‘እስከ ነገ ተቀደሱ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአልና፦ “እስራኤል ሆይ! እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም።”