መጽሐፈ ኢያሱ 7:1-13

መጽሐፈ ኢያሱ 7:1-13 አማ54

የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር በደሉ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ፥ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፥ የእግዚአብሔርም ቁጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዌን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ልኮ፦ ውጡ ምድሪቱንም ሰልሉ ብሎ ተናገራቸው፥ ሰዎቹም ወጡ፥ ጋይንም ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው፦ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፥ ጥቂቶች ናቸውና ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ ለመሄድ አይድከም አሉት። ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፥ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሹ። የጋይም ሰዎች ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ያህል ሰዎችን መቱ፥ ከበሩ እስከ ሸባሪም ድረስ አባረሩአቸው በቁልቁለቱም መቱአቸው፥ የሕዝቡም ልብ ቀለጠ፥ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፥ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ፥ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም አለ፦ ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? በዮርዳኖስ ማዶ መቀመጥን በወደድን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ፥ እስራኤል በጠላቶቻቸው ፊት ከሸሹ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም ከምድር ያጠፋሉ፥ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው? እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፦ ለምን በግምባርህ ተደፍተሃል? ቁም፥ እስራኤል በድሎአል፥ ያዘዝኋቸውንም ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፥ እርም የሆነውንም ነገር ወሰዱ፥ ሰረቁም፥ ዋሹም፥ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፥ የተረገሙ ስለ ሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፥ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ፥ እንዲህም በላቸው፦ እስራኤል ሆይ፥ እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፥ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ተቀደሱ።