ኢያሱ 7:1-13

ኢያሱ 7:1-13 NASV

እስራኤላውያን ግን ዕርም የሆነውን ነገር ለራሳቸው በመውሰድ በደሉ፤ ይህም ከይሁዳ ነገድ የሆነው አካን የከርሚ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የዛራ ልጅ ዕርም ከሆነው ነገር ስለ ወሰደ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ። ኢያሱ ከቤቴል በስተምሥራቅ ካለችው ከቤትአዌን አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ጋይ ከኢያሪኮ ሰዎችን ልኮ፣ “ወደዚያ ውጡ፤ አገሪቱንም ሰልሉ” አላቸው፤ ሰዎቹም ወጥተው ጋይን ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው፣ “ጋይን ለመውጋት ሕዝቡ ሁሉ መሄድ አያስፈልገውም፤ በዚያ ያለው ሕዝብ ጥቂት ስለ ሆነ፣ ከተማዪቱን ለመውጋት ሁለት ወይም ሦስት ሺሕ ሰው ስለሚበቃ ሕዝቡ ሁሉ ወደዚያ በመሄድ አይድከም” አሉት። ስለዚህ ሦስት ሺሕ ያህል ሰው ወጣ፤ ከጋይም ሰዎች ፊት ሸሸ፤ የጋይም ሰዎች እስራኤላውያንንም ከከተማዪቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሽባሪም ድረስ በማባረር ቍልቍለቱ ላይ መቷቸው፤ ከእነርሱም ሠላሳ ስድስት ያህል ሰው ገደሉባቸው። ከዚህ የተነሣም የሕዝቡ ልብ ቀለጠ፤ እንደ ውሃም ፈሰሰ። በዚህ ጊዜ ኢያሱ ልብሱን ቀደደ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፋ፤ የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንደዚሁ አደረጉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ አለ፤ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዮርዳኖስን አሻግረህ ይህን ሕዝብ ወደዚህ ያመጣኸው ለአሞራውያን አሳልፈህ በመስጠት እንዲያጠፉን ነውን? ምነው ሳንሻገር እዚያው ማዶ በቀረን ኖሮ! ጌታ ሆይ፤ እስራኤል በጠላቱ ፊት ሲሸሽ እኔ ምን ልበል? ከነዓናውያንና ሌሎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ ይህን ሲሰሙ ይከብቡናል፤ ስማችንንም ከምድር ገጽ ያጠፉታል፤ እንግዲህ ስለ ታላቁ ስምህ ስትል የምታደርገው ምንድን ነው?” እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ለምን በግንባርህ ተደፋህ? እስራኤል በድሏል፤ እንዲጠብቁ ያዘዝኋቸውን ቃል ኪዳኔን ጥሰዋል፤ ዕርም የሆነውን ነገር ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ዋሽተዋል፤ የወሰዱትንም ከራሳቸው ንብረት ጋራ ደባልቀዋል። እንግዲህ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ለመቋቋም ያልቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ጀርባቸውን አዙረው የሸሹትም ለጥፋት በመዳረጋቸው ነው። ዕርም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ፣ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋራ አልሆንም። “ተነሣ፤ ሕዝቡን ቀድስ፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እስራኤል ሆይ፤ ዕርም የሆነ ነገር በመካከላችሁ ስላለ፣ ይህን ካላስወገዳችሁ ጠላቶቻችሁን ለመቋቋም እንደማትችሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሯልና ለነገ ራሳችሁን ለማዘጋጀት ሰውነታችሁን ቀድሱ።