መጽሐፈ ኢያሱ 7:1-13

መጽሐፈ ኢያሱ 7:1-13 አማ05

እስራኤላውያን ግን የተከለከሉ ነገሮችን በተመለከተ ታማኞች ሆነው አልተገኙም፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው ዓካን፥ የከርሚ ልጅ፥ የዘብዲ የልጅ ልጅ፥ የዛራ ልጅ ከተከለከሉት ነገሮች በመውሰድ በእስራኤል ላይ የእግዚአብሔርን ቊጣ አስነሣ። ኢያሱ በኢያሪኮ ሳለ በቤትአዌን አጠገብ ከቤትኤል በስተምሥራቅ የምትገኘውን “ዐይ” ተብላ የምትጠራውን ከተማና የምድሪቱን አቀማመጥ አጥንተው ይመለሱ ዘንድ ጥቂት ሰዎችን ላከ። ይህንንም በትእዛዙ መሠረት ከፈጸሙ በኋላ፥ ለኢያሱ ከዚህ የሚከተለውን ማስረጃ አቀረቡለት፦ “እነርሱ ጥቂቶች ስለ ሆኑ በዐይ ላይ አደጋ ለመጣል ያለውን ሰው ሁሉ በአጠቃላይ ማዝመት አያስፈልግም፤ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ሰዎች ብቻ ላክ፤ በዚያ ለመዋጋት መላውን ሠራዊት አትላክ።” ስለዚህም ሦስት ሺህ እስራኤላውያን ዘምተው አደጋ ጣሉባት፤ ነገር ግን እነርሱ ከዐይ ወታደሮች ፊት ሸሹ፤ የዐይ ሰዎችም ወደ ሠላሳ ስድስት ያኽል ሰዎችን ገደሉባቸው፤ ከከተማይቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሼባሪዎ ቊልቊለት ድረስ እየገደሉ አባረሩአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀልጦ እንደ ውሃ ፈሰሰ። ኢያሱና የእስራኤል መሪዎች በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ ሐዘናቸውን ለመግለጥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ወዮ! እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህን ሕዝብ ለምን ዮርዳኖስን አሻገርከው? አሞራውያን እንዲያጠፉን ለእነርሱ አሳልፈህ ለመስጠት ነውን? ከዮርዳኖስ ማዶ ብንቀመጥ እንዴት በተሻለን ነበር! አምላክ ሆይ፥ እስራኤል ከጠላቶቹ ፊት ከሸሸ እንግዲህ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንና ሌሎችም በዚህች ምድር የሚኖሩት ሁሉ ይህን ነገር ይሰማሉ፤ ስለዚህም ዙሪያችንን ከበው ሁላችንንም ይፈጁናል፤ ታዲያ ስለ ክብርህ የምታደርገው ምንድን ነው?” እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ስለምን በግንባርህ ወደቅኽ? እስራኤላውያን በድለዋል፤ እንዲጠብቁት ያዘዝኳቸውንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ ከተከለከሉት ነገሮች ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ከራሳቸው ንብረት ጋር በማቀላቀል አታላዮች ሆነዋል። እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን መቋቋም ያልቻሉበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ እነርሱ ራሳቸው እንዲጠፉ ስለ ተፈረደባቸው ከጠላቶች ፊት ወደ ኋላ ይሸሻሉ። እንዲደመሰስ የታዘዘውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ሂድ! ሕዝቡን አንጻ! ‘በመካከላችሁ የተከለከለ ነገር ስላለ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለነገ ራሳችሁን አንጹ!’ ይላል በላቸው። እስራኤል ሆይ! ይህን የተከለከለ ነገር ከመካከልህ ካላስወገድህ በጠላቶችህ ፊት ልትቆም አትችልም።