የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር ታላቅ በደል በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች ላይ ተቈጣ። ኢያሱም ከቤቴል በምሥራቅ በኩል በቤትአዊን አጠገብ ወዳለችው ወደ ጋይ ሰዎችን ከኢያሪኮ ልኮ፥ “ውጡ፤ ጋይንም ሰልሉ” ብሎ ተናገራቸው፤ ሰዎቹም ወጡ፤ ጋይንም ሰለሉ። ወደ ኢያሱም ተመልሰው፥ “ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ያህል ሰው ወጥተው ጋይን ይምቱ እንጂ ሕዝቡ ሁሉ አይውጣ፤ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሁሉ ግን ወደዚያ አትውሰድ፤ ጥቂቶች ናቸውና” አሉት። ሦስት ሺህ ያህል ሰዎችም ወደዚያ ወጡ፤ የጋይም ሰዎች አባረሩአቸው፤ ከፊታቸውም ሸሹ። የጋይ ሰዎችም ከእነርሱ ሠላሳ ስድስት ሰዎችን ገደሉ፤ ከበሩ ጀምረው እስከ አጠፉአቸው ድረስ አባረሩአቸው፤ በቍልቍለቱም ገደሉአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ደነገጠ፤ እንደ ውኃም ሆነ። ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፤ እርሱና የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱም አለ፥ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በአሞሬዎናውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን፥ ታጠፋንም ዘንድ አገልጋይህ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገረ? በዮርዳኖስ ማዶ ተቀምጠን በኖርን ነበር እኮ! ጌታ ሆይ! እስራኤል ጀርባውን ወደ ጠላቶቹ ከመለሰ እንግዲህ ምን እላለሁ? ከነዓናውያንም፥ በምድሪቱም የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፤ ከምድርም ያጠፉናል፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው?” እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፥ “ለምን በግንባርህ ተደፍተሃል? ተነሥ! ሕዝቡ በድለዋል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል፤ እርም ከሆነውም ነገር ሰርቀው ወሰዱ፤ በዕቃቸውም ውስጥ ሸሸጉት። ስለዚህም የእስራኤል ልጆች በጠላቶቻቸው ፊት መቆም አይችሉም፤ የተረገሙ ስለሆኑ በጠላቶቻቸው ፊት ይሸሻሉ፤ እርም የሆነውንም ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር አልሆንም። ተነሣና ሕዝቡን ቀድስ እንዲህም በላቸው፦ ‘እስራኤል ሆይ! እርም የሆነ ነገር በመካከልህ አለ፤ እርምም የሆነውን ነገር ከመካከላችሁ እስክታጠፉ ድረስ በጠላቶቻችሁ ፊት መቆም አትችሉም’ ብሎ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና እስከ ነገ ራሳችሁን አንጹ።
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 7:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች