1 ዜና መዋዕል 16:1-7
1 ዜና መዋዕል 16:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርንም ታቦት ይዘው ገቡ፤ ዳዊትም በተከለላት ድንኳን ውስጥ አኖሩአት፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕትም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። ዳዊትም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ማቅረብ በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ሕዝቡን ባረከ። ለእስራኤልም ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም ቍራጭ ሥጋ፥ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አካፈለ። በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት ያገለግሉ ዘንድ፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ያወድሱት ዘንድ፥ ያመሰግኑትና ያከብሩትም ዘንድ ከሌዋውያን ወገን አቆመ። አለቃውም አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱም ቀጥሎ ዘካርያስ፥ ኢያሔል፥ ሰሜራሞት፥ ይሔኤል፥ ማታትያ፥ ኤልያብ፥ በናያስ፥ አብዲዶም፥ ይዒኤል በመሰንቆና በበገና፥ አሳፍም በጸናጽል ይዘምሩ ነበር። ካህናቱም በናያስና የሕዜኤል በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ሁልጊዜ መለከት ይነፉ ነበር። በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ እጅ እግዝአብሔርን እንዲያመሰግኑ አስቀድሞ ትእዛዝን ሰጠ።
1 ዜና መዋዕል 16:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕትም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ። ከዚያም ለእስራኤል ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ፣ አንዳንድ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ። በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እንዲያገለግሉና ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ልመና፣ ምስጋናና ውዳሴ እንዲያቀርቡ ከሌዋውያን ሰዎች ሾመ፤ አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከርሱ ቀጥሎ ዘካርያስ ሁለተኛ ሆኖ ተሾመ፤ ከዚያም ይዒኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ መቲትያ፣ ኤልያብ፣ በናያስ፣ አቢዳራ፣ ይዒኤል ተሾሙ፤ እነርሱም በመሰንቆና በበገና ይዘምሩ ነበር፤ አሳፍ ደግሞ ጸናጽል የሚጸነጽል ሆኖ ተመደበ። እንዲሁም ካህናቱ በናያስና የሕዚኤል ዘወትር በእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ፊት መለከት እንዲነፉ ተመደቡ። በዚያም ቀን ዳዊት በመጀመሪያ ለአሳፍና ለሥራ ጓደኞቹ ይህን የእግዚአብሔር ምስጋና መዝሙር ሰጠ፤
1 ዜና መዋዕል 16:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔርንም ታቦት ይዘው ገቡ፤ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕትም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። ዳዊትም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ማቅረብ በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ስም ሕዝቡን ባረከ። ለእስራኤልም ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም ቍራጭ ሥጋ፥ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አካፈለ። በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት ያገለግሉ ዘንድ፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ያወድሱት ዘንድ፥ ያመሰግኑትና ያከብሩትም ዘንድ ከሌዋውያን ወገን አቆመ። አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱም በኋላ ዘካርያስ፥ ይዒኤል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ መቲትያ፥ ኤልያብ፥ በናያስ፥ ዖቤድኤዶምና ይዒኤል በመሰንቆና በበገና አሳፍም በጸናጽል ይዘምሩ ነበር። ካህናቱም በናያስና የሕዚኤል በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ሁልጊዜ መለከት ይነፉ ነበር። በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ እጅ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አስቀድሞ ትእዛዝን ሰጠ።
1 ዜና መዋዕል 16:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የቃል ኪዳኑንም ታቦት ወስደው ዳዊት ባዘጋጀው ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ ከዚያም በኋላ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኅብረት መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ ዳዊት መሥዋዕት የማቅረቡን ሥነ ሥርዓት ከጨረሰ በኋላ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ፤ ለእስራኤላውያን ምግብ አከፋፈለ፤ ለወንድም ሆነ ለሴት በእስራኤል ለሚኖር እያንዳንዱ ሰው አንድ ሙልሙል ዳቦ፥ አንድ ቊራጭ ሥጋና ጥቂት ዘቢብ ሰጠ። በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ሆነው ምስጋና፥ ውዳሴና ክብር በማቅረብ ለእግዚአብሔር አምላክ የሚደረገውን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት እንዲመሩ ዳዊት ጥቂት ሌዋውያንን ሾመ። አሳፍ መሪ፥ ዘካርያስም የእርሱ ረዳት ሆነው ተሾሙ፤ ይዒኤል፥ ሸሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ማቲትያ፥ ኤሊአብ፥ በናያ፥ ዖቤድኤዶምና ይዒኤል መሰንቆና በገና ለመደርደር፥ አሳፍም ጸናጽል ለማንሿሿት ተመደቡ፤ በናያና ያሐዚኤል ተብለው የሚጠሩት ሁለት ካህናት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ዘወትር እምቢልታ እንዲነፉ ተመደቡ፤ ዳዊት፥ ለአሳፍና ለቀሩት ሌዋውያን ወገኖቹ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር የማቅረብ ኀላፊነት የሰጣቸው በዚያን ጊዜ ነበር።
1 ዜና መዋዕል 16:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእግዚአብሔርንም ታቦት ይዘው ገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕትም በጌታ ፊት አቀረቡ። ዳዊትም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት አቅርቦ በፈጸመ ጊዜ በጌታ ስም ሕዝቡን ባረከ። ለእስራኤልም ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም ቁራጭ ሥጋ፥ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ። በጌታም ታቦት ፊት እንዲያገለግሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ጌታን እንዲወድሱት፥ እንዲያመሰግኑትና እንዲያከብሩትም ከሌዋውያን ወገን ሾመ። አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱም ቀጥሎ መሰንቆና በገና ይጫወቱ የነበሩት ዘካርያስ፥ ይዒኤል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ መቲትያ፥ ኤልያብ፥ በናያስ፥ ዖቤድ-ኤዶም፥ ይዒኤል ነበሩ፤ አሳፍም የጸናጽልን ድምፅ ያሰማ ነበረ። ካህናቱም በናያስና የሕዚኤል በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ሁልጊዜ መለከት ይነፉ ነበር። በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ አንደበት ጌታን እንዲያመሰግኑ አስቀድሞ ትእዛዝን ሰጠ።