አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:1-7

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:1-7 አማ05

የቃል ኪዳኑንም ታቦት ወስደው ዳዊት ባዘጋጀው ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ ከዚያም በኋላ በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኅብረት መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር አቀረቡ፤ ዳዊት መሥዋዕት የማቅረቡን ሥነ ሥርዓት ከጨረሰ በኋላ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ፤ ለእስራኤላውያን ምግብ አከፋፈለ፤ ለወንድም ሆነ ለሴት በእስራኤል ለሚኖር እያንዳንዱ ሰው አንድ ሙልሙል ዳቦ፥ አንድ ቊራጭ ሥጋና ጥቂት ዘቢብ ሰጠ። በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ሆነው ምስጋና፥ ውዳሴና ክብር በማቅረብ ለእግዚአብሔር አምላክ የሚደረገውን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት እንዲመሩ ዳዊት ጥቂት ሌዋውያንን ሾመ። አሳፍ መሪ፥ ዘካርያስም የእርሱ ረዳት ሆነው ተሾሙ፤ ይዒኤል፥ ሸሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ማቲትያ፥ ኤሊአብ፥ በናያ፥ ዖቤድኤዶምና ይዒኤል መሰንቆና በገና ለመደርደር፥ አሳፍም ጸናጽል ለማንሿሿት ተመደቡ፤ በናያና ያሐዚኤል ተብለው የሚጠሩት ሁለት ካህናት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ዘወትር እምቢልታ እንዲነፉ ተመደቡ፤ ዳዊት፥ ለአሳፍና ለቀሩት ሌዋውያን ወገኖቹ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር የማቅረብ ኀላፊነት የሰጣቸው በዚያን ጊዜ ነበር።