1 ዜና መዋዕል 16

16
1ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕትም#16፥1 በዚህና በቍጥር 2 ላይ በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል። በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። 2ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ። 3ከዚያም ለእስራኤል ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ፣ አንዳንድ ሙዳ ሥጋና#16፥3 የዕብራይስጡ ቃል ጥፍጥፍ ተምር ተብሎም ሊተረጐም ይችላል። አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ።
4እግዚአብሔር ታቦት ፊት እንዲያገለግሉና ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ልመና፣ ምስጋናና ውዳሴ እንዲያቀርቡ ከሌዋውያን ሰዎች ሾመ፤ 5አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከርሱ ቀጥሎ ዘካርያስ ሁለተኛ ሆኖ ተሾመ፤ ከዚያም ይዒኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ መቲትያ፣ ኤልያብ፣ በናያስ፣ አቢዳራ፣ ይዒኤል ተሾሙ፤ እነርሱም በመሰንቆና በበገና ይዘምሩ ነበር፤ አሳፍ ደግሞ ጸናጽል የሚጸነጽል ሆኖ ተመደበ። 6እንዲሁም ካህናቱ በናያስና የሕዚኤል ዘወትር በእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ፊት መለከት እንዲነፉ ተመደቡ።
የዳዊት የምስጋና መዝሙር
16፥8-22 ተጓ ምብ – መዝ 105፥1-15
16፥23-33 ተጓ ምብ – መዝ 96፥1-13
16፥34-36 ተጓ ምብ – መዝ 106፥1106፥47-48
7በዚያም ቀን ዳዊት በመጀመሪያ ለአሳፍና ለሥራ ጓደኞቹ ይህን የእግዚአብሔር ምስጋና መዝሙር ሰጠ፤
8 እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤
ሥራውንም በሕዝቦች መካከል አሳውቁ።
9ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤
ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ፤
10በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤
እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ልባቸው ሐሤት ያድርግ።
11 እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤
ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ።
12ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣
ታምራቱንና የሰጠውንም ፍርድ አስታውሱ፤
13እናንተ የባሪያው የእስራኤል ዘሮች፣
እናንተ የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች።
14እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤
ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው፤
15ኪዳኑን ለዘላለም፣
ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ ያስባል።
16ከአብርሃም ጋራ የገባውን ቃል ኪዳን፣
ለይሥሐቅም የማለውን መሐላ።
17ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፤
ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤
18እንዲህ ሲል፣ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣
የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ”
19ቍጥራቸው ገና ጥቂት ሳለ፣
በርግጥ ጥቂትና መጻተኞች ሳሉ፣
20ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝብ፣
ከአንዱም መንግሥት ወደ ሌላው ተንከራተቱ።
21ማንም እንዲጨቍናቸው አልፈቀደም፤
ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤
22እንዲህ ሲል፤ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤
በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።”
23ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤
ማዳኑንም ዕለት ዕለት ዐውጁ።
24ክብሩን ለአሕዛብ ተናገሩ፤
ድንቅ ሥራዎቹን ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ።
25 እግዚአብሔር ታላቅ ነውና፤ ውዳሴውም ብዙ ነው፤
ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ ይገባዋል።
26የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።
27ክብርና ግርማ በፊቱ ናቸው፤
ብርታትና ደስታም በማደሪያው ስፍራ።
28የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር ስጡ፤
ክብርንና ብርታትን ለእግዚአብሔር ስጡ።
29ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤
መባ ይዛችሁ በፊቱ ቅረቡ፤
በቅድስናውም ክብር ለእግዚአብሔር#16፥29 ወይም፣ ከክብሩ ጋራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።
30ምድር ሁሉ በፊቱ ትንቀጥቀጥ፤
ዓለም በጽኑ ተመሥርታለች፤ አትናወጥምም።
31ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድርም ሐሤት ታድርግ፤
በአሕዛብም መካከል፤ “እግዚአብሔር ነገሠ!” ይበሉ።
32ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ ያስተጋባ፤
ሜዳዎችና በርሷ ላይ ያሉ ሁሉ በደስታ ይዘምራሉ።
33ያን ጊዜ የዱር ዛፎች በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤
በደስታ ይዘምራሉ፤
በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና።
34ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
35“የመዳናችን አምላክ ሆይ አድነን፤
ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣ በምስጋናህም እንድንከብር ሰብስበን፤
ከአሕዛብም መካከል ታደገን”
ብላችሁ ጩኹ።
36ከዘላለም እስከ ዘላለም፣
ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “አሜን፤ እግዚአብሔር ይመስገን” አሉ።
37ዳዊትም ለእያንዳንዱ ቀን በተመደበው መሠረት፣ ዘወትር እንዲያገለግሉ አሳፍንና የሥራ ባልደረቦቹን በዚያው በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተዋቸው። 38እንዲሁም ዖቤድኤዶምና ስድሳ ስምንቱ የሥራ ባልደረቦቹ ዐብረዋቸው እንዲያገለግሉ በዚያው ተዋቸው። የኤዶታም ልጅ ዖቤድኤዶምና ሖሳ የቅጥሩ በር ጠባቂዎች ሆኑ።
39ዳዊት ካህኑን ሳዶቅንና የሥራ ባልደረቦቹን ካህናት በገባዖን ከፍተኛ ቦታ ላይ በሚገኘው በእግዚአብሔር ድንኳን ተዋቸው፤ 40የተዋቸውም ለእስራኤል በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈው ሁሉ፣ በመሠዊያው ላይ የሚቀርበውን የሚቃጠል መሥዋዕት ጧትና ማታ በየጊዜው እንዲያቀርቡ ነው። 41እንዲሁም “ፍቅሩ ለዘላለም ነውና” እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና እንዲያቀርቡ ኤማንና ኤዶታም እንዲሁም ተመርጠውና ስማቸው ተመዝግቦ የተመደቡ ሌሎችም ዐብረዋቸው ነበሩ። 42ድምፀ መለከቱንና ጸናጽሉን ለማሰማት፣ ደግሞም መንፈሳዊ መዝሙር ሲዘመር ለሚጠቀሙባቸው ሌሎች መሣሪያዎች ኀላፊዎቹ ኤማንና ኤዶታም ነበሩ፤ የኤዶታምም ልጆች በሩን እንዲጠብቁ ተመድበው ነበር።
43ከዚያም ሕዝቡ ተነሣ፤ እያንዳንዱም ወደየቤቱ ሄደ። ዳዊትም ቤተ ሰቡን ለመባረክ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ