1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:1-7
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 16:1-7 መቅካእኤ
የእግዚአብሔርንም ታቦት ይዘው ገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕትም በጌታ ፊት አቀረቡ። ዳዊትም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት አቅርቦ በፈጸመ ጊዜ በጌታ ስም ሕዝቡን ባረከ። ለእስራኤልም ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም ቁራጭ ሥጋ፥ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ። በጌታም ታቦት ፊት እንዲያገለግሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ጌታን እንዲወድሱት፥ እንዲያመሰግኑትና እንዲያከብሩትም ከሌዋውያን ወገን ሾመ። አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱም ቀጥሎ መሰንቆና በገና ይጫወቱ የነበሩት ዘካርያስ፥ ይዒኤል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ መቲትያ፥ ኤልያብ፥ በናያስ፥ ዖቤድ-ኤዶም፥ ይዒኤል ነበሩ፤ አሳፍም የጸናጽልን ድምፅ ያሰማ ነበረ። ካህናቱም በናያስና የሕዚኤል በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ሁልጊዜ መለከት ይነፉ ነበር። በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ አንደበት ጌታን እንዲያመሰግኑ አስቀድሞ ትእዛዝን ሰጠ።

