ኤርምያስ 31:23-40
ኤርምያስ 31:23-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ ሀገር በከተሞችዋ፦ የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክህ የሚል ነገርን እንደ ገና ይናገራሉ። በይሁዳ ከተሞችና በሀገሩ ሁሉ ከገበሬዎችና መንጋን ይዘው ከሚዞሩ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ይገኛሉ። የተጠማችውን ነፍስ ሁሉ አርክቻለሁና፥ የተራበችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና። ስለዚህ ነቃሁ፤ ተመለከትሁም፤ እንቅልፌም ጣፈጠኝ። “በእስራኤል ቤትና በይሁዳ ቤት የሰው ዘርና የእንስሳ ዘር የምዘራበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። እንዲህም ይሆናል፤ አፈርሳቸውና ክፉ አደርግባቸው ዘንድ እንደ ተጋሁባቸው፥ እንዲሁ እሠራቸውና እተክላቸው ዘንድ እተጋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። በዚያ ዘመን ሰው ዳግመኛ እንዲህ አይልም፦ አባቶች ጮርቃ የወይን ፍሬ በሉ፤ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ ጮርቃውን የወይን ፍሬ የሚበላም ሁሉ ጥርሶቹ ይጠርሳሉ። “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከግብፅ ሀገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን ዕወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።” ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን፥ ጨረቃንና ከዋክብትንም በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ዘር በፊቴ ሕዝብ እንዳይሆን ለዘለዓለም ይቀራል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰማይ እጅግ ከፍ ቢል፥ የምድርም መሠረት ፈጽሞ ዝቅ ቢል በዚያ ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ፥ የእስራኤልን ዘር ሁሉ እንቃለሁ ይላል እግዚአብሔር። “ከአናምሄል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ከተማ ለእግዚአብሔር የሚሠራበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር። መጠንዋ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፤ ወደ ጎዓትም ይዞራል። የአስሬሞትም ሸለቆ ሁሉ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል እስካለው እስከ ፈረስ በር ማዕዘን ድረስ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘለዓለም አይነቀልም፤ አይፈርስምም።
ኤርምያስ 31:23-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምርኳቸውን በመለስሁላቸው ጊዜ፣ እነርሱ በይሁዳ ምድርና በከተሞቿ፣ ‘አንተ የጽድቅ ማደሪያ ቅዱስ ተራራ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ!’ የሚል አነጋገር እንደ ገና ይጠቀማሉ። ገበሬዎችና ዘላን ከብት አርቢዎች በይሁዳና በከተሞቿ በአንድነት ይኖራሉ። የዛለችውን ነፍስ ዐድሳለሁ፤ የደከመችውንም አበረታለሁ።” በዚህ ጊዜ ከእንቅልፌ ነቅቼ ዙሪያዬን ተመለከትሁ፤ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆኖልኝ ነበር። “እነሆ፤ የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት” ይላል እግዚአብሔር፤ “በሰውና በእንስሳት ዘር የምሞላበት ጊዜ ይመጣል፤ ልነቅላቸውና ላፈርሳቸው፣ ልገለብጣቸውና ላጠፋቸው፣ መከራም ላመጣባቸው እንደ ተጋሁ ሁሉ፣ ላንጻቸውና ልተክላቸው ደግሞ እተጋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ፣ “ ‘አባቶች በበሉት ጐምዛዛ የወይን ፍሬ፣ የልጆች ጥርስ ጠረሰ’ የሚለውን ምሳሌ አይናገሩም። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል፤ ጐምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሰው ሁሉ የራሱን ጥርስ ይጠርሳል። “ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋራ” ይላል እግዚአብሔር፣ “አዲስ ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል። ከግብጽ አወጣቸው ዘንድ፣ እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣ ከአባቶቻቸው ጋራ እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ የእነርሱ ባል ሆኜ ሳለሁ፣ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና።” ይላል እግዚአብሔር። “ነገር ግን ከዚያ ጊዜ በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “ሕጌን በአእምሯቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ከእንግዲህ ማንም ሰው ባልንጀራውን፣ ወይም ወንድሙን፣ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤ ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ፣ ሁሉም እኔን ያውቁኛልና፤” ይላል እግዚአብሔር። “በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስብም።” በቀን እንድታበራ፣ ፀሓይን የመደበ፣ በሌሊት እንዲያበሩ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ያዘዛቸው፣ የሞገዱ ድምፅ እንዲተምም፣ ባሕሩን የሚያናውጥ፣ ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነ እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሥርዐት በፊቴ ከተሻረ፣” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚያ ጊዜ የእስራኤልም ዘር በፊቴ፣ መንግሥት መሆኑ ለዘላለም ይቀራል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በላይ ያሉትን ሰማያትን መለካት፣ በታችም ያሉትን የምድር መሠረቶች መመርመር ከተቻለ፣ በዚያ ጊዜ የእስራኤልን ዘር ሁሉ፣ ስላደረጉት ነገር ሁሉ እጥላቸዋለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር። “እነሆ ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማእዘኑ በር ድረስ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ይህች ከተማ ለእግዚአብሔር የምትሠራበት ጊዜ ይመጣል፤ መለኪያ ገመዱም ከዚያ ጀምሮ በቀጥታ ወደ ጋሬብ ኰረብታ፣ ዐልፎም ወደ ጎዓ ይዘረጋል። ሬሳና ዐመድ የሚጣልበት ሸለቆ በሙሉ፣ በምሥራቅ በኩል የቄድሮንን ሸለቆ ይዞ እስከ ፈረስ በር የሚደርሰው ደልዳላ ቦታ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ከተማዪቱ አትነቀልም፤ አትፈርስምም።”
ኤርምያስ 31:23-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ፦ የጽድቅ ማደሪያ ሆይ፥ የቅድስና ተራራ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ የሚልን ነገር እንደ ገና ይናገራሉ። በይሁዳ ከተሞችና በአገሩ ሁሉ ከገበሬዎችና መንጋን ይዘው ከሚዞሩ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ይገኛሉ። የደከመችውን ነፍስ አርክቻለሁና፥ ያዘነችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና። ከዚህም በኋላ ነቃሁ ተመለከትሁም፥ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆነልኝ። የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት በሰው ዘርና በእንስሳ ዘር የምዘራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። እንዲህም ይሆናል፥ አፈርሳቸውና ክፉ አድርግባቸው ዘንድ እንደ ተጋሁባቸው፥ እንዲሁ እሠራቸውና እተክላቸው ዘንድ እተጋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። በዚያ ዘመን ሰው ዳግመኛ እንዲህ አይልም፦ አባቶች ጨርቋ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፥ ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፥ መራራውን የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ ጥርሶቹ ይጠርሳሉ። እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፥ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፥ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና። ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያን ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ዘር በፊቴ ሕዝብ እንዳይሆን ለዘላለም ይቀራል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ በላይ ቢከነዳ፥ የምድርም መሠረት በታች ቢመረመር፥ በዚያን ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ የእስራኤልን ዘር ሁሉ እጥላለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ከተማ ለእግዚአብሔር የሚሠራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። የተለካበትም ገመድ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፥ ወደ ጎዓም ይዞራል። የሬሳም ሸለቆ ሁሉ የአመድም እርሻ ሁሉ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል እስካለው እስከ ፈረሰ በር ማዕዘን ድረስ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፥ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘላለም አይነቀልም አይፈርስምም።
ኤርምያስ 31:23-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡን ወደ አገራቸው በመለስኩ ጊዜ በይሁዳና በከተሞቹ እንደገና ‘አንቺ የእውነት ማደሪያ የሆንሽ ቅድስት ተራራ እግዚአብሔር ይባርክሽ’ ይላሉ። ‘ይሁዳና ከተሞቹ ሁሉ የሕዝብ መኖሪያ ይሆናሉ፤ ምድርን የሚያርሱ ገበሬዎችና መንጋን የሚጠብቁ እረኞች በዚያ ይገኛሉ፤ የደከሙትን ሁሉ ኀይላቸው እንዲታደስ አደርጋለሁ፤ በረሀብ ዝለው የነበሩትንም ምግብ በመስጠት አጠግባቸዋለሁ፤ ስለዚህም በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ‘ተኝተን ስንነቃ ታደስን’ ይላሉ። “እኔ እግዚአብሔር የእስራኤልንና የይሁዳን ምድር በሕዝብና በእንስሶች የምሞላበት ጊዜ ይመጣል። እነርሱን ለመንቀልና ለማፍረስ፥ ለመገለባበጥና ለማጥፋት፥ ለመደምሰስም እከታተል የነበርኩትን ያኽል፥ እነርሱን እንደገና ለመትከልና ለማነጽም እከታተላለሁ። በዚያ ዘመን፥ ‘አባቶች የበሉት ጎምዛዛ የሆነ የወይን ፍሬ፥ የልጆችን ጥርስ አጠረሰ’ እየተባለ የሚነገረው ምሳሌ ይቀራል። ይህ መሆኑ ቀርቶ ጎምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሰው ሁሉ የገዛ ራሱን ጥርስ ብቻ ያጠርሳል፤ እያንዳንዱም በገዛ ራሱ ኃጢአት ይሞታል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ከእስራኤል ሕዝብና ከይሁዳ ሕዝብ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል፤ ይህም ቃል ኪዳን እነርሱን ከግብጽ ለማውጣት እጃቸውን በያዝኩ ጊዜ እንደ ገባሁት ቃል ኪዳን ያለ አይደለም፤ እኔ አምላካቸው ብሆንም እንኳ እነርሱ ቃል ኪዳኔን አልጠበቁም፤ እኔም ችላ አልኳቸው፤ እነሆ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ ባልንጀራውንም ሆነ ወንድሙን የሚያስተምር ማንም አይኖርም፤ ከትልቁ ጀምሮ እስከ ትንሹ ሁሉም ያውቁኛል፤ በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም አላስታውስባቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” ፀሐይን በቀን እንዲያበራ የሚያደርገው፥ ጨረቃና ከዋክብት በሌሊት እንዲያበሩ ሥርዓትን የወሰነላቸው፥ ባሕሩን በማዕበል እንዲናወጥ የሚቀሰቅሰው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ስሙም የሠራዊት አምላክ ነው። የተፈጥሮ ሥርዓት ጸንቶ እስከ ኖረ ድረስ እስራኤል በፊቱ ሕዝብ ሆና የምትኖር መሆንዋን የሚገልጥ ተስፋ ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን በሠሩት በደል ምክንያት ይጥላቸዋል ማለት የሚቻለው የሰማይ ስፋቱ ተለክቶ፥ የምድርም መሠረቶች ሁሉ ተመርምረው ለመታወቅ ቢችሉ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከሐናንኤል መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ እስከ ማእዘኑ የቅጽር በር ድረስ ኢየሩሳሌም የእኔ ከተማ ሆና የምትታነጽበት ጊዜ ይመጣል። የወሰኑም መስመር ከማእዘኑ ቅጥር በር ወደ ጋሬብ ኰረብታ ይሄድና ወደ ጎዓ ይዞራል። በድንና ዐመድ የሚጣልበት መላው ሸለቆ በምሥራቅ በኩል እስከ ፈረስ በር ድረስ እንኳ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከተማይቱም እንደገና ከቶ አትፈርስም፤ አትደመሰስምም።”
ኤርምያስ 31:23-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ፦ ‘የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! ጌታ ይባርክህ’ የሚልን ቃል እንደገና ይናገራሉ። የይሁዳና የከተሞችዋ ሕዝብ ሁሉ፥ ገበሬዎችና ከመንጋቸም ጋር የሚዞሩ በአንድነት በዚያ ይቀመጣሉ። የደከመችውን ነፍስ አርክቻለሁና፥ የዛለችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና።” ከዚህም በኋላ ነቃሁ ተመለከትሁም፥ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆነልኝ። “የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት በሰው ዘርና በእንስሳ ዘር የማራባበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል ጌታ። እንዲህም ይሆናል፤ እነርሱን ልነቅላቸውና ልሰባብራቸው፥ ላፈርሳቸውና ላጠፋቸው፥ ክፉም ላደርግባቸው እንደ ተጋሁ፥ እንዲሁ ልሠራቸውና ልተክላቸው እተጋለሁ፥ ይላል ጌታ። በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ እንዲህ አይሉም፦ ‘አባቶች የሚጎመዝዝ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፤’ ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ መራራውን የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ ጥርሶቹ የተጠረሱ ይሆናሉ።” “እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የማደርግበት ወራት ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ እጃቸውን ይዤ ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ አደረግሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እኔ ገዢአቸው ብሆንም እንኳ ያን ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፥ ይላል ጌታ። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የማደርገው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ ‘ጌታን እወቅ’ ብሎ ከእንግዲህ ወዲህ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል ጌታ። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስምና።” ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን የማይዛነፍ ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ጽኑ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል ጌታ፥ በዚያን ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ትውልድ በፊቴ ሕዝብ የመሆኑ ነገር ለዘለዓለም ያበቃለታል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ በላይ ያለው ሰማይ ቢለካ፥ በታችም ያለው የምድር መሠረት ቢመረመር፥ በዚያን ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ የእስራኤልን ትውልድ በሙሉ እጥላለሁ፥ ይላል ጌታ።” “ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ለጌታ ከተማ የሚሠራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል ጌታ። የመለኪያውም ገመድ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፥ ከዚያም ወደ ጎዓም ይዞራል። የሬሳና የአመድ ሸለቆ ሁሉ፥ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ ያለው የትልም እርሻ ሁሉ፥ በምሥራቅም በኩል እስካለው እስከ ፈረሰ በር ማዕዘን ድርስ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘለዓለም አይነቀልም አይፈርስምም።”