ትንቢተ ኤርምያስ 31:23-40

ትንቢተ ኤርምያስ 31:23-40 መቅካእኤ

የእስራኤል አምላክ የሠርዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ አገር በከተሞችዋ፦ ‘የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! ጌታ ይባርክህ’ የሚልን ቃል እንደገና ይናገራሉ። የይሁዳና የከተሞችዋ ሕዝብ ሁሉ፥ ገበሬዎችና ከመንጋቸም ጋር የሚዞሩ በአንድነት በዚያ ይቀመጣሉ። የደከመችውን ነፍስ አርክቻለሁና፥ የዛለችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና።” ከዚህም በኋላ ነቃሁ ተመለከትሁም፥ እንቅልፌም ጣፋጭ ሆነልኝ። “የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት በሰው ዘርና በእንስሳ ዘር የማራባበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል ጌታ። እንዲህም ይሆናል፤ እነርሱን ልነቅላቸውና ልሰባብራቸው፥ ላፈርሳቸውና ላጠፋቸው፥ ክፉም ላደርግባቸው እንደ ተጋሁ፥ እንዲሁ ልሠራቸውና ልተክላቸው እተጋለሁ፥ ይላል ጌታ። በዚያ ዘመን ሰዎች ዳግመኛ እንዲህ አይሉም፦ ‘አባቶች የሚጎመዝዝ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፤’ ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ መራራውን የወይን ፍሬ የሚበላ ሁሉ ጥርሶቹ የተጠረሱ ይሆናሉ።” “እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የማደርግበት ወራት ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ እጃቸውን ይዤ ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ አደረግሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እኔ ገዢአቸው ብሆንም እንኳ ያን ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፥ ይላል ጌታ። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የማደርገው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ ‘ጌታን እወቅ’ ብሎ ከእንግዲህ ወዲህ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል ጌታ። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስምና።” ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን የማይዛነፍ ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ጽኑ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል ጌታ፥ በዚያን ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ትውልድ በፊቴ ሕዝብ የመሆኑ ነገር ለዘለዓለም ያበቃለታል። ጌታ እንዲህ ይላል፦ በላይ ያለው ሰማይ ቢለካ፥ በታችም ያለው የምድር መሠረት ቢመረመር፥ በዚያን ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ የእስራኤልን ትውልድ በሙሉ እጥላለሁ፥ ይላል ጌታ።” “ከሐናንኤል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ለጌታ ከተማ የሚሠራበት ዘመን፥ እነሆ፥ ይመጣል፥ ይላል ጌታ። የመለኪያውም ገመድ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፥ ከዚያም ወደ ጎዓም ይዞራል። የሬሳና የአመድ ሸለቆ ሁሉ፥ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ ያለው የትልም እርሻ ሁሉ፥ በምሥራቅም በኩል እስካለው እስከ ፈረሰ በር ማዕዘን ድርስ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘለዓለም አይነቀልም አይፈርስምም።”