የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ምርኮአቸውን በመለስሁ ጊዜ በይሁዳ ሀገር በከተሞችዋ፦ የጽድቅ ማደሪያ ሆይ! የቅድስና ተራራ ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክህ የሚል ነገርን እንደ ገና ይናገራሉ። በይሁዳ ከተሞችና በሀገሩ ሁሉ ከገበሬዎችና መንጋን ይዘው ከሚዞሩ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ይገኛሉ። የተጠማችውን ነፍስ ሁሉ አርክቻለሁና፥ የተራበችውንም ነፍስ ሁሉ አጥግቤአለሁና። ስለዚህ ነቃሁ፤ ተመለከትሁም፤ እንቅልፌም ጣፈጠኝ። “በእስራኤል ቤትና በይሁዳ ቤት የሰው ዘርና የእንስሳ ዘር የምዘራበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። እንዲህም ይሆናል፤ አፈርሳቸውና ክፉ አደርግባቸው ዘንድ እንደ ተጋሁባቸው፥ እንዲሁ እሠራቸውና እተክላቸው ዘንድ እተጋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። በዚያ ዘመን ሰው ዳግመኛ እንዲህ አይልም፦ አባቶች ጮርቃ የወይን ፍሬ በሉ፤ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ በገዛ በደሉ ይሞታል፤ ጮርቃውን የወይን ፍሬ የሚበላም ሁሉ ጥርሶቹ ይጠርሳሉ። “እነሆ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከግብፅ ሀገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር። ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን ዕወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኀጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።” ስሙ የሠራዊት ጌታ የሚባል፥ ፀሐይን በቀን፥ ጨረቃንና ከዋክብትንም በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ፥ እንዲተምሙም የባሕርን ሞገዶች የሚያናውጥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕግ ከፊቴ ቢወገድ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ጊዜ ደግሞ የእስራኤል ዘር በፊቴ ሕዝብ እንዳይሆን ለዘለዓለም ይቀራል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰማይ እጅግ ከፍ ቢል፥ የምድርም መሠረት ፈጽሞ ዝቅ ቢል በዚያ ጊዜ ስላደረጉት ነገር ሁሉ፥ የእስራኤልን ዘር ሁሉ እንቃለሁ ይላል እግዚአብሔር። “ከአናምሄል ግንብ ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ ከተማ ለእግዚአብሔር የሚሠራበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር። መጠንዋ ወደ ጋሬብ ኮረብታ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄዳል፤ ወደ ጎዓትም ይዞራል። የአስሬሞትም ሸለቆ ሁሉ እስከ ቄድሮን ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል እስካለው እስከ ፈረስ በር ማዕዘን ድረስ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለዘለዓለም አይነቀልም፤ አይፈርስምም።
ትንቢተ ኤርምያስ 31 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 31:23-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች