የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡን ወደ አገራቸው በመለስኩ ጊዜ በይሁዳና በከተሞቹ እንደገና ‘አንቺ የእውነት ማደሪያ የሆንሽ ቅድስት ተራራ እግዚአብሔር ይባርክሽ’ ይላሉ። ‘ይሁዳና ከተሞቹ ሁሉ የሕዝብ መኖሪያ ይሆናሉ፤ ምድርን የሚያርሱ ገበሬዎችና መንጋን የሚጠብቁ እረኞች በዚያ ይገኛሉ፤ የደከሙትን ሁሉ ኀይላቸው እንዲታደስ አደርጋለሁ፤ በረሀብ ዝለው የነበሩትንም ምግብ በመስጠት አጠግባቸዋለሁ፤ ስለዚህም በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ‘ተኝተን ስንነቃ ታደስን’ ይላሉ። “እኔ እግዚአብሔር የእስራኤልንና የይሁዳን ምድር በሕዝብና በእንስሶች የምሞላበት ጊዜ ይመጣል። እነርሱን ለመንቀልና ለማፍረስ፥ ለመገለባበጥና ለማጥፋት፥ ለመደምሰስም እከታተል የነበርኩትን ያኽል፥ እነርሱን እንደገና ለመትከልና ለማነጽም እከታተላለሁ። በዚያ ዘመን፥ ‘አባቶች የበሉት ጎምዛዛ የሆነ የወይን ፍሬ፥ የልጆችን ጥርስ አጠረሰ’ እየተባለ የሚነገረው ምሳሌ ይቀራል። ይህ መሆኑ ቀርቶ ጎምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሰው ሁሉ የገዛ ራሱን ጥርስ ብቻ ያጠርሳል፤ እያንዳንዱም በገዛ ራሱ ኃጢአት ይሞታል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ከእስራኤል ሕዝብና ከይሁዳ ሕዝብ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል፤ ይህም ቃል ኪዳን እነርሱን ከግብጽ ለማውጣት እጃቸውን በያዝኩ ጊዜ እንደ ገባሁት ቃል ኪዳን ያለ አይደለም፤ እኔ አምላካቸው ብሆንም እንኳ እነርሱ ቃል ኪዳኔን አልጠበቁም፤ እኔም ችላ አልኳቸው፤ እነሆ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ ባልንጀራውንም ሆነ ወንድሙን የሚያስተምር ማንም አይኖርም፤ ከትልቁ ጀምሮ እስከ ትንሹ ሁሉም ያውቁኛል፤ በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም አላስታውስባቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” ፀሐይን በቀን እንዲያበራ የሚያደርገው፥ ጨረቃና ከዋክብት በሌሊት እንዲያበሩ ሥርዓትን የወሰነላቸው፥ ባሕሩን በማዕበል እንዲናወጥ የሚቀሰቅሰው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ስሙም የሠራዊት አምላክ ነው። የተፈጥሮ ሥርዓት ጸንቶ እስከ ኖረ ድረስ እስራኤል በፊቱ ሕዝብ ሆና የምትኖር መሆንዋን የሚገልጥ ተስፋ ይሰጣል፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን በሠሩት በደል ምክንያት ይጥላቸዋል ማለት የሚቻለው የሰማይ ስፋቱ ተለክቶ፥ የምድርም መሠረቶች ሁሉ ተመርምረው ለመታወቅ ቢችሉ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከሐናንኤል መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ እስከ ማእዘኑ የቅጽር በር ድረስ ኢየሩሳሌም የእኔ ከተማ ሆና የምትታነጽበት ጊዜ ይመጣል። የወሰኑም መስመር ከማእዘኑ ቅጥር በር ወደ ጋሬብ ኰረብታ ይሄድና ወደ ጎዓ ይዞራል። በድንና ዐመድ የሚጣልበት መላው ሸለቆ በምሥራቅ በኩል እስከ ፈረስ በር ድረስ እንኳ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከተማይቱም እንደገና ከቶ አትፈርስም፤ አትደመሰስምም።”
ትንቢተ ኤርምያስ 31 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 31:23-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች