ኢሳይያስ 49:14-26

ኢሳይያስ 49:14-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ጽዮን ግን፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትቶ​ኛል፤ ጌታም ረስ​ቶ​ኛል” አለች። “በውኑ ሴት፥ ልጅ​ዋን ትረ​ሳ​ለ​ችን? ከማ​ኅ​ፀ​ንዋ ለተ​ወ​ለ​ደ​ውስ አት​ራ​ራ​ምን? ሴት ይህን ብት​ረሳ፥ እኔ አን​ቺን አል​ረ​ሳ​ሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ ግን​ቦ​ች​ሽን ሣልሁ፤ አን​ቺም ሁል​ጊዜ በፊቴ ነሽ። ከአ​ፈ​ረ​ሱሽ በኋላ ፈጥ​ነሽ ትታ​ነ​ጺ​ያ​ለሽ፤ ያፈ​ረ​ሱሽ ከአ​ንቺ ይወ​ጣሉ። ዐይ​ን​ሽን አን​ሥ​ተሽ በዙ​ሪ​ያሽ ተመ​ል​ከቺ፤ እነ​ዚህ ሁሉ ተሰ​ብ​ስ​በው ወደ አንቺ ይመ​ጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነ​ዚ​ህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለ​ብ​ሻ​ቸ​ዋ​ለሽ፤ እንደ ሙሽ​ራም ትጐ​ና​ጸ​ፊ​አ​ቸ​ዋ​ለሽ ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። ፈር​ሰ​ሻ​ልና፥ ፈጽ​መ​ሽም ጠፍ​ተ​ሻ​ልና በአ​ንቺ ለሚ​ኖሩ ሰዎች ዛሬ ጠባብ ትሆ​ኚ​ባ​ቸ​ዋ​ለሽ፤ ያጠ​ፉ​ሽም ከአ​ንቺ ይር​ቃሉ። አጥ​ተ​ሻ​ቸው የነ​በ​ሩት ልጆ​ች​ሽም በጆ​ሮሽ፦ ስፍራ ጠብ​ቦ​ና​ልና የም​ን​ቀ​መ​ጥ​በት ቦታ አስ​ፊ​ልን ይላሉ። አን​ቺም በል​ብሽ፦ የወ​ላድ መካን ሆኛ​ለ​ሁና፥ እኔም መበ​ለት ነኝና እነ​ዚ​ህን ማን ወለ​ደ​ልኝ? እነ​ዚ​ህ​ንስ ማን አሳ​ደ​ጋ​ቸው? እነሆ፥ ብቻ​ዬን ቀርቼ ነበር፤ እነ​ዚ​ህስ ከወ​ዴት መጡ?” ትያ​ለሽ። ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ እጄን ወደ አሕ​ዛብ አነ​ሣ​ለሁ፤ ዓር​ማ​ዬ​ንም ወደ ደሴ​ቶች አቆ​ማ​ለሁ፤ ወን​ዶች ልጆ​ች​ሽ​ንም በብ​ብ​ታ​ቸው ታቅ​ፈው ያመ​ጡ​አ​ቸ​ዋል፤ ሴቶች ልጆ​ች​ሽ​ንም በጫ​ን​ቃ​ቸው ላይ ይሸ​ከ​ሙ​አ​ቸ​ዋል። ነገ​ሥ​ታ​ትም አሳ​ዳ​ጊ​ዎች አባ​ቶ​ችሽ ይሆ​ናሉ፤ እቴ​ጌ​ዎ​ቻ​ቸ​ውም ሞግ​ዚ​ቶ​ችሽ ይሆ​ናሉ፤ ግን​ባ​ራ​ቸ​ው​ንም ወደ ምድር ዝቅ አድ​ር​ገው ይሰ​ግ​ዱ​ል​ሻል፤ የእ​ግ​ር​ሽ​ንም ትቢያ ይል​ሳሉ፤ እኔም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ሆንሁ ታው​ቂ​ያ​ለሽ፤ እኔ​ንም በመ​ተ​ማ​መን የሚ​ጠ​ባ​በቁ አያ​ፍ​ሩም።” በውኑ ምር​ኮን ከኀ​ይ​ለኛ እጅ መቀ​ማት ይቻ​ላ​ልን? በግፍ የተ​ማ​ረ​ከስ ይድ​ና​ልን? እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን እን​ዲህ ይላል፥ “በኀ​ያ​ላን የተ​ማ​ረኩ ይወ​ሰ​ዳሉ፤ የጨ​ካ​ኞ​ችም ብዝ​በዛ ያመ​ል​ጣል፤ እኔም ፍር​ድ​ሽን እፈ​ር​ድ​ል​ሻ​ለሁ፤ ልጆ​ች​ሽ​ንም አድ​ና​ለሁ። የአ​ስ​ጨ​ና​ቂ​ዎ​ች​ሽ​ንም ሥጋ​ቸ​ውን ይበ​ላሉ፤ እንደ ጣፋጭ ወይን ጠጅም ደማ​ቸ​ውን ጠጥ​ተው ይሰ​ክ​ራሉ፤ ሥጋ ለባ​ሹም ሁሉ እኔ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መድ​ኀ​ኒ​ት​ሽና ታዳ​ጊሽ፥ የያ​ዕ​ቆ​ብን ኀይል የም​ደ​ግፍ እንደ ሆንሁ ያው​ቃሉ።”

ኢሳይያስ 49:14-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጽዮን ግን፣ “እግዚአብሔር ትቶኛል፤ ጌታም ረስቶኛል” አለች። “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም! እነሆ፤ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ፤ ቅጥሮችሽ ምን ጊዜም በፊቴ ናቸው። ወንዶች ልጆችሽ ፈጥነው ይመለሳሉ፤ ያፈራረሱሽም ከአንቺ ይሸሻሉ። ዐይንሽን ቀና አድርጊ፤ ዙሪያውንም ተመልከቺ፤ ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝ፤ እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊያቸዋለሽ” ይላል እግዚአብሔር። “ፈራርሰሽ ባድማ ብትሆኚ፣ ምድርሽ ፈጽሞ ቢጠፋ፣ ዛሬ ለሕዝብሽ ጠባብ ብትሆኚም እንኳ፣ የዋጡሽ ከአንቺ ይርቃሉ። በሐዘንሽ ዘመን የወለድሻቸው ልጆች፣ ጆሮሽ እየሰማ፣ ‘ይህ ቦታ በጣም ጠብቦናል፤ የምንኖርበት በቂ ስፍራ ስጪን’ ይሉሻል። በልብሽም እንዲህ ትያለሽ፣ ‘እነዚህን የወለደልኝ ማን ነው? እኔ ሐዘንተኛና መካን፣ የተሰደድሁና የተጠላሁ ነበርሁ፤ እነዚህን ማን አሳደጋቸው? ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ ታዲያ፣ እነዚህ ከየት መጡ?’ ” ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ አሕዛብን በጥቅሻ እጣራለሁ፤ ዐርማዬንም ለሕዝቦች ከፍ አደርጋለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽን በዕቅፋቸው ያመጡልሻል፤ ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ይሸከሙልሻል። ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ፣ እቴጌዎቻቸው ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤ የእግርሽን ትቢያ ይልሳሉ፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፤ እኔን ተስፋ የሚያደርጉም አያፍሩም።” ከተዋጊ ብዝበዛ ማስጣል፣ ከጨካኝስ ምርኮኞችን ማዳን ይቻላልን? እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ “ከተዋጊዎች ላይ ምርኮኞች በርግጥ ይወሰዳሉ፤ ከጨካኞችም ላይ ምርኮ ይበዘበዛል፤ ከአንቺ ጋራ የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፤ ልጆችሽንም እታደጋለሁ። አስጨናቂዎችሽ የራሳቸውን ሥጋ እንዲበሉ አደርጋቸዋለሁ፤ በወይን ጠጅ እንደሚሰከር ሁሉ፣ በገዛ ደማቸው ይሰክራሉ። ከዚያም የሰው ዘር ሁሉ፣ እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽ፣ ታዳጊሽም የያዕቆብ ኀያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።”

ኢሳይያስ 49:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ጽዮን ግን፦ እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁል ጊዜ በፊቴ አሉ። ልጆችሽ ይፈጥናሉ፥ ያፈረሱሽና ያወደሙሽ ከአንቺ ዘንድ ይወጣሉ። ዓይንሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፥ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጎናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር። ባድማሽና ውድማሽ ወናም የሆነው ምድርሽ ከሚኖሩብሽ የተነሣ ዛሬ ጠባብ ትሆናለችና፥ የዋጡሽም ይርቃሉና። የወላድ መካን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱልሽ ልጆችሽ በጆሮሽ፦ ስፍራ ጠብቦኛልና እቀመጥ ዘንድ ቦታ አስፊልኝ ይላሉ። አንቺም በልብሽ፦ የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁና ተቅበዝብዤአለሁምና እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፥ እነዚህስ ወዴት ነበሩ? ትያለሽ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፥ ዓላማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፥ ወንዶች ልጆችሽንም በብብታቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል። ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዝቶችሽ ይሆናሉ፥ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም። በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይወሰዳልን? ወይስ የጨካኙ ምርኮኞች ያመልጣሉን? እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦ በኃያላን የተማረኩ ይወሰዳሉ፥ የጨካኞችም ብዝበዛ ያመልጣል፥ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁ። አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፥ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሠክራሉ፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብ ኃያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።

ኢሳይያስ 49:14-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የኢየሩሳሌም ሕዝብ ግን፥ “እግዚአብሔር ትቶናል፤ ጌታዬም ረስቶናል” አሉ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልሳል፦ “እናት የምታጠባውን ልጅዋን ልትረሳ ትችላለችን? ወይስ ለወለደችው ልጅ አትራራምን? እርስዋ እንኳ ብትረሳ እኔ ግን እናንተን አልረሳም። ኢየሩሳሌም ሆይ! እነሆ፥ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ፤ ቅጥሮችሽንም ዘወትር አስታውሳለሁ። “አንቺን የሚገነቡ ፈጣኖች ናቸው፤ ያወደሙሽ ግን ከአንቺ ርቀው ይሄዳሉ። ቀና ብለሽ ዙሪያሽን ተመልከቺ፤ ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ እንዲህ እላለሁ፦ ‘ሁሉንም እንደ ልብስ ትለብሺአቸዋለሽ፤ ሙሽራ በጌጣጌጥ እንደምታጌጥ አንቺም በእነርሱ ታጌጪአለሽ።’ “ ‘ፈራርሰሽ ባድማ እንድትሆኚ፥ ምድርሽም ጠፍ እንዲሆን ቢያደርጉሽም እንኳ፥ አሁን አንቺ ተመልሰው ለሚመጡ ለነዋሪዎችሽ ጠባብ ትሆኚአለሽ፤ የአፈራረሱሽም ከአንቺ ርቀው ይሄዳሉ።’ በስደት የተወለዱ ልጆችሽ ‘ይህ ቦታ ለእኛ በጣም ጠባብ ስለ ሆነ የምንኖርበት ሰፊ ቦታ ስጪን’ ይሉሻል። ከዚህ በኋላ አንቺም በልብሽ እንዲህ ትያለሽ፦ ‘እነዚህን ልጆች ማን ወለደልኝ? ብዙ ልጆቼን አጥቼና የወላድ መኻን ሆኜ ነበር፤ ተሰድጄ፥ ተቀባይነትም አጥቼ ነበር፤ ታዲያ እነዚህን ልጆች ያሳደጋቸው ማነው? እኔ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እንግዲህ እነዚህ ልጆች ከወዴት መጡ?’ ” ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ወንዶች ልጆችሽን በክንዳቸው፥ ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ተሸክመው ያመጡ ዘንድ ለመንግሥታት ምልክት እሰጣለሁ፤ ለሕዝቦችም ዐርማን አነሣለሁ። ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፤ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል። የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ ከዚህም የተነሣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቂአለሽ፤ የእኔን ርዳታ ለማግኘት የሚጠባበቁ ከቶ አያፍሩም።” ከጀግና እጅ ምርኮን መውሰድ ይቻላልን? ወይስ ከጨካኝ ሰው እጅ ምርኮኛን ማስለቀቅ ይቻላልን? እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦ “አንቺን የሚቃወሙሽን እኔ ስለምቃወም፥ ጀግና የያዘው ምርኮኛ እንኳ ይወሰዳል፤ ከጨካኝ እጅም ምርኮ ይለቀቃል፤ እኔም ልጆችሽን አድናለሁ። ጨቋኞችሽ የገዛ ሥጋቸውን እንዲበሉ አደርጋለሁ፤ በወይን ጠጅ እንደሚሰክሩ የገዛ ደማቸውን ጠጥተው እንዲሰክሩ አደርጋለሁ። ከዚህም የተነሣ እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽና ታዳጊሽ የእስራኤል ኀያል አምላክ መሆኔን የዓለም ሕዝብ ሁሉ ያውቃል።”

ኢሳይያስ 49:14-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጽዮን ግን፦ “ጌታ ትቶኛል፥ እርሱ ረስቶኛል” አለች። በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ የተወለደው ሕጻን ልጇን ትረሳለች? ርህራሄ አልባስ እስክመሆን ትደርሳለች? አዎን፥ እርሷ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም። እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ። ልጆችሽ ይፈጥናሉ፥ ሊያፈረሱሽና ሊያወደሙሽ ከአንቺ ይወጣሉ። ዓይንሽን አንስተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጎናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል ጌታ። ባድማሽና ውድማሽ ወናም የሆነው ምድርሽ ከሚኖሩብሽ የተነሣ ዛሬ ጠባብ ትሆናለችና፥ የዋጡሽም ይርቃሉ። የወላድ መካን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱልሽ ልጆችሽ በጆሮሽ፦ “ስፍራ ጠብቦኛልና እድንቀመጥ ቦታ አስፊልን” ይላሉ። አንቺም በልብሽ፦ “የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁ፥ ተቅበዝብዤአለሁ፥ እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እነዚህስ ወዴት ነበሩ?” ትያለሽ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፥ ዓላማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በዕቅፋቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል። ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዝቶችሽ ይሆናሉ፤ ግንባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እኔም ጌታ እንደሆንኩ ታውቂያለሽ፤ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም። በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይነጠቃል? ወይስ ከጨካኙ ምርኮኞችን ማስመለጥ ይቻላል? ጌታ ግን እንዲህ ይላል፦ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁና፥ በኃያላን የተማረኩ እንኳን ይወሰዳሉ፥ የጨካኞች ብዝበዛም ቢሆን ያመልጣል። አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፥ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሠክራሉ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ ጌታ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብ ኃያል እንደሆንሁ ያውቃል።